ትራምፕ ጆ ባይደን ወደ ዋይት ሐውስ እንዲገቡ ዝግጅት እንዲደረግ ተስማሙ

ተመራጩ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ዶናልድ ትራምፕ መደበኛ በሆነ መንገድ ጆ ባይደን ወደ ቤተ መንግሥት እንዲገቡ ሂደቶች ከወዲሁ እንዲጀመሩ ስምምነታቸውን ገለጹ።

የሽግግር ሂደቱን ለሚመራው መሥሪያ ቤትም ሥራውን መጀመር እንደሚችል ትራምፕ በይፋ ተናግረዋል።

ትራምፕ እንዳሉት የሥልጣን ሽግግር ጉዳዮችን የሚከታተለው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት ለጆ ባይደን ማድረግ ያለበትን ሁሉ ሊየደርግ ይገባል ብለዋል።

ነገር ግን ይህ ማለት መሸነፌን ተቀብያለው ማለት አይደለም፥ በፍርድ ቤት የተጭበረበረውን ምርጫ እፋለመዋለሁ ሲሉም አክለዋል።

ሽግግር ላይ የሚሰራው ጄኔራል ሰርቪስ አድሚኒስትሬሽን መሥሪያ ቤት ይፋ እንዳደረገው ጆ ባይደን በማያሻማ ሁኔታ ተመራጩ ፕሬዝደንት ናቸው ብሏል። ጂኤስኤ በሚል ምህጻር የሚታወቀው የዚህ መሥሪያ ቤት ሹም ኤሚሊ መርፊ እንደተናገሩት መሥሪያ ቤታቸው 6 ሚሊዮን ዶላር ለሽግግሩ መድቧል።

መሥሪያ ቤቱ ይህንን መናገሩን ተከትሎ ደግሞ ፔንታገን ለባይደን አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ይህ የትራምፕ መለሳለስ የመጣው ጆ ባይደን በሚሺጋን ግዛት አሸናፊ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ይፋዊ ሰርተፊኬት ማግኘታቸውን ተከትሎ ነው።

የትራምፕን መለሳለስ የጆ ባይደን ቡድን በበጎ ተመልክቶታል።

ትናንት ጆ ባይደን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና የብሔራዊ ደህንነት ቡድን አባላትን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። ብዙዎቹ በኦባማ አስተዳደር ጊዜ ያገለገሉ ሰዎች ስብስብ ነው።

አንቶኒ ብሊንከን ትልቁን ሥልጣን እንዲቆናጠጡ በባይደን የታጩትም ትናንትና ነበር። አንተኒ ብሊንከን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። በኦባማ ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ጆን ኬሪ የአየር ንብረት ለውጥ ልዩ መልእክተኛ ተደርገው ታጭተዋል።

ጃኔት የለን ደግሞ የመጀመርያዋ የአሜሪካ ግምጃ ቤት (ገንዘብ ሚኒስትር) ዋና ጸሐፊ ተደርገዋል።

በአሜሪካ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዶናልድ ትራምፕ አሸናፊ ለሆነ ፕሬዝዳንታዊ እጩ የእንኳን ደስ ያለህ መልእክት ለማስተላለፍና ሽንፈታቸውን ለመቀበል ተቸግረው ቆይተዋል።

ከሰሞኑ ግን የገዛ ወዳጆቻቸው ሳይቀር "ደስ አይልም" እያሏቸው ነው። ትራምፕ ከገዛ ፓርቲያቸው ጭምር ሽንፈታቸውን እንዲቀበሉ ጫና እየመጣባቸው ነው።

ትናንት የቴነሲ ሴናተር ላማር አሌክሳንደር ለትራምፕ ባስተላለፉት መልእክት "ዶናልድ ከራስህ ይልቅ ለአገርህ ክብር ቅድሚያ ስጥ" ብለዋቸዋል።

ጡረታ እየወጡ ያሉት እኚህ ሴናተር በዚህ መልእክታቸው እንዲህ ብለዋል፥ "የሕዝብ አገልጋይ ስትሆን ሕዝብ የሚያስታውሰው መጨረሻ ያደረከውን ነገር ነው"