ደቡብ አፍሪካዊቷ መምህርት ለዓለም ምርጥ መምህር ሽልማት ታጨች

ታትሟል

በዚህ ዓመት በሚካሄደው ዓለም አቀፉ ምርጥ መምህር ሽልማት 10 መምህራን በመጨረሻው ዙር ዝርዝር ውስጥ ገብተዋል፤ ከእነዚህ መካከል አንዷ ደቡብ አፍሪካዊቷ መምህርት ሞኩዱ ሳይንቲያ ማቻባ ናት።

በዘንድሮው ውድድር ከ140 አገራት 12 ሺህ ተወዳዳሪዎች የተሳተፉበት ሲሆን፤ ሞኩዱ ከአስሩ ዝርዝር ውስጥ የገባችው ይህንን ፈታኝ ውድድር አልፋ ነው።

ሞኩዱ ሳይንቲያ ማቻባ በደቡብ አፍሪካ ሰሜናዊ ክፍል ሊምፖፖ በሚገኝ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የምታስተምረው።

መምህርቷ ተማሪዎቿን ስለምታስተምርበት መንገድና ተማሪዎቿ የትምህርት ፍላጎታቸውን ለማሳደግ የተከተለችውን መንገድ ለቢቢሲ ኒውስ ዴይ እንዲህ ስትል ተናግራለች።

"እኔ ያስተዋወቅኩት ፕሮጀክት ላይ የተመሰረተ የማስተማሪያ ዘዴ ነው። ተግባራዊና በሙከራ ላይ የተመሰረቱ ትምህርቶችን ለመስጠት ግብዓቱ አለን። ከዚህም በተጨማሪ አገር በቀል እውቀቶችን እጠቀማለሁ። በመሆኑም አገር በቀል በሆነ መንገድ ነገሮችን እንዴት መስራት እንደሚቻል ለማስተማርም የማኅበረሰብ አባላትን አሳትፌያለሁ። በዚህም ተማሪዎቹ በራስ መተማመናቸውን እንዲያጎለብቱ ማድረግ ችያለሁ።"

መምህር ማቻባ ተማሪዎቿ በትልቁ እንዲያልሙ እና ዩኒቨርሲቲ መግባት የቻሉት ተመልሰው መጥተው እንዲያመሰግኗት እንደምታበረታታቸው ተናግራለች።

በዚህ የምርጥ መምህራን ሽልማት ባለፈው ዓመት ተሸላሚ የነበረው የፍራንሲስካ ካቶሊካዊ እምነት ተከታይ የሆነው ኬንያዊው መምህር ፒተር ታቢቺ ነበር።

ፒተር በወቅቱ ከነበሩት የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በዋይት ሐውስ የመገናኘት እድልም አግኝቶ ነበር።

ፒተር ታቢቺ ከኬንያ ዋና መዲና ናይሮቢ በስተሰሜን ምዕራብ 188 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሳይንስ አስተማሪ ሲሆን የኬንያ ድሃ ተማሪዎችን ለመርዳት ከወር ገቢው 80 በመቶውን በመለገስ ይታወቃል።

ፒተር ለሙያው ባለው ፍቅርና በተማሪዎቹ ላይ ያሳደረው ጠንካራ እምነት፤ ከፍተኛ የሆነ የግብዓት ችግር ያለበት ትምህርት ቤቱን አገር አቀፍ የሳይንስ ውድድር አሸናፊ እንዲሆን ማስቻሉ ይነገራል።

በየዓመቱ በሚዘጋጀው ዓለም አቀፍ የምርጥ መምህራን ሽልማት አሸናፊ ለሞያቸው ላበረከቱት አስተዋፅኦ የ1 ሚሊየን ዶላር ሽልማት ይበረከትላቸዋል።