ፖምፔዮ በዌስት ባንክ የእስራኤላዊያን ሰፈራ ያልተጠበቀ ጉብኝት አደረጉ

ፖምፒዮ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ በእስራኤል ወረራ በተያዘው የዌስት ባንክ የአይሁዳውያን የሰፈራ አካባቢ ከዚህ በፊት ያልተደረገ ጉብኝት አካሄዱ።

በዚህም አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን መሰል ጉብኝት ሲያደርግ ፖምፔዮ የመጀመሪያ ናቸው።

የፖምፔዮ የሳጎት ጉብኝት ለዓመታት የቆየውን የአሜሪካን አቋም በመቀልበስ ሰፈራው ዓለም አቀፍ ሕግን የማይቃረን መሆኑን ከገለጹ ከአንድ ዓመት በኋላ የተደረገ ነው።

የፖምፔዮ ንግግር ለወደፊቱ ነፃ መንግሥት ሲመሰርቱ ቦታው እንደሚገባቸው የሚገልጹትን እና ሰፈራውን የሚቃወሙትን ፍልስጤማውያንን አስቆጥቶ ነበር።

ፖምፒዮ የጎላን ተራሮችንም በተመሳሳይ ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ዓመት የጎላን ተራሮች የእስራኤል ሉዓላዊ ግዛት መሆናቸውን ጠቁመው ነበር። እስራኤል አካባቢውን እ.አ.አ በ1967 የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከሶሪያ የነጠቀች ሲሆን እ.አ.አ በ1981 ከግዛቷ ጋር ቀላቅላዋለች።

ፖምፔዮ ወደ እስራኤል ያቀኑት ትናንት ረቡዕ ሲሆን በጥር ወር ስልጣናቸውን ከመልቀቃቸው በፊት ወደ አገሪቱ ያደረጉት የመጨረሻ ጉዞቸው ሊሆን ይችላል ተብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዛሬ ሐሙስ ጠዋት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በኢየሩሳሌም ተወያይተዋል።

ፖምፔዮ በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ እስራኤልን ለማግለል እየተካሄደ ያለውን ዘመቻ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፀረ-ሴማዊ ሲል እንደሚፈርጀው ገልጸዋል። ይህ በንግድና ኢንቨስትመት ላይ ያተኮረው የማግለል ዘመቻ እስራኤል በፍልስጤም ላይ በምታራምደው ፖሊሲዎች ምክንያት ሙሉ በሙሉ የሚቃወማት ነው።

ፖምፔዮ በመቀጠልም ራማላህ አቅራቢያ ወደ ሚገኘው የአይሁድ ሰፈራ ጣቢያ በማቅናት ሳጎት የወይን መጥመቂያን ጎብኝተዋል። በአካባቢው አንድ ወይን ለክብራቸው ሲባል በፖምፔዮ ስም ቀደም ብሎ ተሰይሟል።

"ለዓመታት የውጭ ጉዳይ ሚንስቴሩ ስለሰፈራ ጣቢያዎች የተሳሳተ አመለካከት ተከትሏል። ለዚህ ልዩ ቦታ የታሪክ ዕውቅና ያልሰጠ ዕይታን ወስዷል። ከዛሬ ጀምሮም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ተገቢና ትክክለኛ በሆነ መንገድ ለሚከናወኑ ሰፈራዎች ዕውቅና ይሰጣል" ሲሉ ፖምፔየ በኢየሩሳሌም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

እስራኤል በ1967 በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን ከተቆጣጠረች ወዲህ በተገነቡ ሰፈራዎች ከ600 ሺህ በላይ አይሁዶች ይኖሩበታል።

አብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሰፈራዎቹ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር ሕገ-ወጥ እንደሆኑ ቢቆጥሩትም እስራኤል ግን ታስተባብላለች።

የፍልስጤም መሪዎች ባለፈው ሳምንት የአሜሪካን ከፍተኛ ዲፕሎማት ወደ ሳጎት የወይን ጠጅ ማምረቻ ጉብኝት ካደረጉ ግጭት ቀስቃሽ ሊሆን ይችላል በሚል አስጠንቅቀዋል።

በአካባቢው ጉብኝቱን በመቃወም ሰልፎች ተካሂደዋል። ረቡዕ ዕለት በደርዘን የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በኢየሩሳሌም እና ራማላህ መካከል በሚገኘው አል-ቢሬህ በተባለ ቦታ ሰልፎችን አካሂደዋል።

ፖምፔዮ በሰፈራዎቹ ላይ የሰጡትን መግለጫ አዲስ ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ይቀለብሱታል ተብሎ ይጠበቃል።

ሆኖም ትራምፕ በ 2017 ኢየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ ናት ሲሉ እውቅና የሰጡበትን ውሳኔ እንደማይቀለብሱ ተናግረዋል።