በርማ፡የአንግ ሳን ሱቺ ፓርቲ 'በአብላጫ' ድምፅ አሸነፈ

ታትሟል

የበርማ ገዢ ፓርቲ ናሺናል ሊግ ፎር ዲሞክራሲ (ኤንኤል ዲ) መንግሥት ለመመስረት የሚያስፈልገውን የፓርላማ ወንበሮችን ማግኘት እንደቻለ ከምርጫ ውጤቶች መረዳት ችለናል።

ኤንኤልዲ እስካሁን ድረስ 346 የፓርላማ ወንበሮችን ማግኘት የቻለ ሲሆን መንግሥት ለመመስረት ከሚያስፈልገው 322 ወንበሮችም በላይ ነው።

ፓርቲው በመሪዋ አንግ ሳን ሱቺም የሚመራ ነው።

ሆኖም በወታደራዊ ኃይል የሚመራው የተቃዋሚ ፓርቲ ምርጫው እንደገና እንዲደረግ ጥያቄ አቅርቧል።

የኤንኤልዲ ፓርቲ ቃለ አቀባይ ሞንይዋ አንግ ሺን እንዳሉት ፓርቲው 'በከፍተኛ' ድምፅ ማሸነፉ የህዝቡን ድጋፍ አሳይ ነው ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

አክለውም ፓርቲው ብሄራዊ መንግሥት ለመመስረት እየሰራ ነው ብለዋል።

ፓርቲው አናሳ ብሄሮችን የሚወክሉ ፓርቲዎች ጋርም አብሮ ለመስራት እንደሚጋብዝ አስታውቋል።

ከአምስት አመት በፊት ሲያሸንፍ እንዲህ አይነት ጥሪዎችን አላደረገም ነበር።

ህንድ፣ ጃፓንና ሲንጋፖር ፖርቲው በማሸነፉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

በዚህ አመት ምርጫ ለፓርቲው ኤንኤልዲም ሆነ ለመሪዋ አንግ ሳን ሱቺ ህዝቡ ድጋፍ ይሰጥ ይሆን የሚል ጥያቄን አጭሯል። ይሄም ከሮሂንጃ ቀውስ ጋር በተያያዘ ነው።

ኤንኤልዲ አሁንም ቢሆን በበርማ ከፍተኛ ድጋፍ ያለው ቢሆንም በአለም አቀፍ ዘንድ ግን ከፍተኛ ውግዘትን አትርፏል። በተለይም መሪዋ አንግ ሳን ሱቺ ለቀውሱ የሰጡት ምላሽ በከፍተኛ ሁኔታ አስተችቷቸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የዘር እልቂት ብሎ በጠራው ፍጅት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊም ሮሂንጃዎች ወታደራዊ ጭፍጨፋን በመፍራት ተሰደዋል።

ከሶስት አመታት በተፈጠረው በዚህ ፍጅት በርማ ታጣቂዎችን ኢላማ ነው ያደረግኩት በማለት የተከራከረች ሲሆን መሪዋም አንግ ሳን ሱቺ ይህንኑ ደግፈው ቆመዋል።

በሮሂንጃ ሙስሊሞች ላይ የተፈጠረው ይህ ቀውስም በርካታ ታዛቢዎች የምርጫ ውጤቱን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ እንዲከቱት አድርጓቸዋል።