አይቮሪኮስት፡ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ሰላም ለማውረድ ተስማሙ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በቅርቡ ከተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ለሳምንታት የቀጠለውን አመጽ ተከትሎ የአይቮሪኮስት ፕሬዝዳንት አላሳኔ ኦታራ እና ዋነኛ ተቀናቃኛቸው ሄንሪ ኮናን ቤዲዬ ሰላም ለማውረድ መስማማታቸውን አስታወቁ።
ሁለቱ ፖለቲከኞች በንግድ ከተማዋ አቢጃን ከተገናኙ በኋላ በቅርበት አብረው እንደሚሰሩና ንግግራቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል። ስምምነቱንም ለአገሪቱ ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው ብለውታል።
መንግሥት እንደሚለው እስካሁን በመላው አገሪቱ በተቀሰቀሰው አመጽ የ85 ዜጎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ግን የሟቾቹ ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል እየገለጹ ነው።
ፕሬዝዳንት አላሳኔ ኦታራ በአከራካሪ ሁኔታ ምርጫውን ማሸነፋቸው ለበርካታ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ደጋፊዎቻቸው አልተዋጠላቸውም።
አገሪቱን በመምራት ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት አላሳን ኦታራን ሊተኩ ይችላሉ የተባሉት ግለሰብ በድንገት ሕይወታቸው ማለፉን ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ በድጋሚ ለሦስተኛ ጊዜ እወዳደራለሁ በማለታቸው ነሐሴ ወር ላይ በተቀሰቀሰ አመፅ ቢያንስ 14 ሰዎች ተገድለው ነበር።
በአይቮሪኮስት ሕገ መንግሥት መሠረት አንድ ፕሬዝዳንት ለሁለት የስልጣን ዘመን ይቆያል። ሁለት ጊዜ የተመረጡት ፕሬዝዳንት ኦታራ ስልጣናቸውን እንደሚለቁ ተናግረው ነበር።
ባሳለፍነው ሳምንት የተካሄደው ምርጫ ላይ አንሳተፍም ያሉት የአይቮሪኮስት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ሰላማዊ ሽግግር ያስፈልጋል ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ፓስካል አፊ ናጉሴን እና ሄነሪ ኮናን ቤዲዬ እንዳሉት፤ ፕሬዘዳንት አላሳኔ ኦታራ ለሦስተኛ ጊዜ ለምርጫ መቅረባቸው ሕገ ወጥ ነው። የፕሬዘዳንቱ ደጋፊዎች ግን ይህንን አይቀበሉም።
እአአ 2016 ላይ ሕገ መንግሥቱ እንደተለወጠና የፕሬዝዳንቱ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን እንደማይቆጠር ይናገራሉ።
ምርጫው ሲካሄድ በርካታ የምርጫ ጣቢያዎች በተቃዋሚዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ተቃዋሚዎች መንገድ የዘጉባቸው ግዛቶችም ነበሩ። ተቃዋሚዎቹን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተተኩሷል። ዋነኛ የተቃዋሚ ፖርቲ መሪዎች ሕዝቡ “አምባገነናዊ አገዛዝን ይግታ” ሲሉም ተደምጠዋል።
የአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን በበኩሉ ከ22,381 ጣቢያዎች መካከል ዝግ የነበሩት 50 ብቻ ናቸው ብሏል። 35,000 የጸጥታ ኃይሎች የምርጫ ቁሳቁስ በማሰራጨት እና ሰላም በማስጠበቅ እንደተሳተፉ ተነግሯል።
ፕሬዘዳንቱ “የሰው ሕይወት እየጠፋበት ያለው ተቃውሞ መቆም አለበት። አይቮሪኮስት ሰላም ትሻለች” ሲሉ ለተቃዋሚዎች ተናግረውም ነበር።
ፕሬዝዳንት አላሳኔ ኦታራ እና ዋነኛ ተቀናቃኛቸው ሄንሪ ኮናን ቤዲዬ ከተወያዩ በኋል ፕሬዝዳንቱ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ መጠይቅ "በድጋሚ መተማመን ላይ ደርሰናል" ሲሉ ተደምጠዋል። ነገር ግን ሁለቱ ተቀናቃኞች አልተጨባበጡም።













