ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ዴንማርክ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንስሳትን ልትገድል ነው
ዴንማርክ በኮሮናቫይረስ ፍራቻ 17 ሚሊዮን ገደማ እንስሳቶቿን ልትገድል እንደምትችል አሳውቃለች።
ሚንክ የተባሉት እንስሳት ኮሮናቫይረስን ወደ ሰው ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ በመፍራት ነው ዴንማርክ ሚሊዮኖችን ለመግደል የወሰነችው።
ዴንማርክ ሚንክ ከተሰኙት እንስሳት የሚገኘውን ፀጉር በማምረት ከዓለም አንደኛ ስትሆን ዋነኛ ገበያዋ ደግሞ ቻይና እና ሆንግ ኮንግ ናቸው።
በርካታ ሚንኮች በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነው እንስሳቱን መግደል የተያዘው።
ኔዘርላንድስና ስፔንም በእነዚህ እንስሳት ላይ ኮሮናቫይረስ አግኝተዋል።
ነገር ግን በጣም በርካታ እንስሳት የታመሙባት ዴንማርክ ስትሆን አስራ ሁለት ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስቴር ፍሬዴሪክሰን ሁኔታው እጅግ እጀግ አሳሳቢ ነው ብለዋል።
የእንስሳቱን ጅምላ ግድያ እንዲያግዙ የዳኒሽ ፖሊስና ወታደሮች ተጠርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሉት ከእንስሳቱ ወደ ሰው የሚተላለፈው ቫይረስ አሁን በመበልፀግ ላይ ያለውን ክትባት መቋቋም የሚችል ነው።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከጀመረ ወዲህ ዴንማርክ ከ52 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙባትና 733 ሰዎች እንደሞቱባት አሳውቃለች።
በየዓመቱ ቢያንስ 50 ሚሊዮን ሚንኮች በቻይና፣ ዴንማርክ፣ ኔዘርላንድስና ፖላንድ ለፀጉራቸው ሲባል ይረባሉ።
ቫይረሱ ከእነዚህ እንስሳት ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ከታወቀ ወዲህ በርካታ ሃገራት እንስሳቱን መግደል ጀምረዋል።
እንስሳት ልክ እንደ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ የተለያዩ ምልክቶች ያሳያሉ።
ጉዳዩን እጅግ አሳሳቢ ያደረገው ነገር ቫይረሱ ከእንስሳቱ ወደ ሰው እንደ አዲስ ከተሰራጨ ክትባት ተቋቋሚ ሊሆን ይችላል የሚለው ነው።
የዓለም የጤና ድርጅት እንስሳቱን በማስወገዱ ላይ ከዴንማርክ መንግሥት ጋር እየሠራ ነው ተብሏል
ባለፈው ሐምሌ ስፔን በኮሮናቫይረስ ፍራቻ 100 ሺህ ሚንኮችን ገድላለች።