የካናዳው ትሩዶ 'ከፈረንሳይ ጎን ነኝ' እያሉ ነው

ታትሟል

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ከፈረንሳይ አቻቸው ጋር መክረዋል።

ትሩዶ፤ በቅርቡ ፈረንሳይ ውስጥ የተከሰቱትን የሽብር ጥቃቶች በማስታወስ ሃገራቸው ካናዳ ከፈረንሳይ ጎን እንደቆመች አስረግጠዋል።

አንድ አስተማሪ የነብዩ ሞሐመድን የካርቱን ምስል ለሕፃናት ተማሪዎች ካሳየ በኋላ አንገቶ ተቀልቶ መገደሉ ይታወሳል።

ጠ/ሚ ትሩዶ ሃሳብ በነፃ መግለፅን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት ከካናዳና ፈረንሳይ ትችት ገጥሟቸዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑዔል ማክሮን የካርቱን ምስሉ መታተምን ደግፈው የሰጡት አስተያየት በሙስሊም ሃገራት ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።

በአንዳንድ ሃገራት የፈረንሳይን ምርቶች አትግዙ የሚል ጥሪ ቀርቦም ነበር።

ትሩዶ ምን አሉ?

ትሩዶ በቅርቡ በፈረንሳይ የደረሱትን ጥቃቶች አውግዘዋል።

ኒስ በተባለችው ከተማ በስለት የደረሰውን አደጋ ጨምሮ ፈረንሳይ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሶስት ጥቃቶችን አስተናግዳለች።

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር የነብዩ ሞሐመድ ምስል በካርቱን መታተሙ አግባብ ነው በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ "ሃሳብን በነፃ መግለፅ ገደብ ሊኖረው አይገባም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

"ለሌሎች ክብር መስጠት እንደሚገባን እሙን ነው፤ የምኖንርባትን ምድር አብረውን የሚጋሩ ሰዎች አለአግባብ መጉዳት ተገቢ አይደለም።"

"ለምሳሌ ትያትር ቤት ውስጥ ዘለን ተነስተን እሳት ብለን መጮህ አግባብ አይደለም፤ ሁሉም ነገር ገደብ አለው" ብለዋል።

ማክሮንስ ምን አሉ?

የፈረንሳዩ ፕሬዝደነት ከካናደዋ የኪዩቤክ ግዛት አስተዳዳሪ ፍራንሷ ሌጎ ጋር ዕለተ ረቡዕ በስልክ ሽቦ ተገናኝተው መክረዋል።

አስተዳዳሪው ፈረንሳዩ ውስጥ የደረሱ ጥቃቶችን እንደሚያወግዙ አሳውቀዋል።

ትሩዶና ማክሮን ግን ዕለተ ሐሙስ ነው በስልክ ያወሩት።

የፈረንሳዩ ማክሮንና የካናዳው ትሩዶ አስተሳሰብና ግብራቸው አንድ ነው ተብለው ይታማሉ። ለዚህም ነው የካናዳው ትሩዶ ከፈረንሳይ ጎን የቆሙት ይላሉ ተንታኞች።

"የሃሳብ ነፃነትና የመናገር ነፃነትን መጠበቅ አስፈላጊ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል ትሩዶ።

ሁለቱ መሪዎች በችግርና መከራ አብረው ለመሥራት ተስማምተው ነው ስልኩ የተዘጋው ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ ቢሮ አሳውቋል።