ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ቱሪስት ያጣችው ኢንዶኔዥያ በ22 ዓመት ያልታየ የምጣኔ ሀብት ድቀት ገጠማት
ኢንዶኔዥያ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በ22 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ የምጣኔ ሀብት ድቀት ገጥሟታል።
ከደቡብ ምሥራቅ እስያ ትልቁ ምጣኔ ኃብት የነበራት ኢንዶኔዥያ ካለፈው ዓመት አንጻር እድገቷ በ3.49% ቀንሷል። ተመሳሳይ የምጣኔ ሀብት ውድቀት የታየው እአአ በ1998 ነበር።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ 3.5 ሚሊዮን ዜጎች ሥራ አጥ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተሰግቷል። ኢንዶኔዥያ ከቀጠናው አገሮች በከፍተኛ ሁኔታ በወረርሽኙ ተጠቅታለች።
ግብርና የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት የጀርባ አጥንት ቢሆንም፤ ዋነኛ የገቢ ምንጯ ግን ቱሪዝም ነው። በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ባሊ፣ የሩዝ ማሳ እና የሂንዱ ቤተ እምነቶችን ይጎበኛሉ።
ኢንዶኔዥያ በወረርሽኙ ሳቢያ ድንበሯን ከዘጋች ወዲህ ግን የቱሪስት ፍሰቱ ቆሟል። ከሐምሌ እስከ መስከረም የታየው 3.49% የምጣኔ ሀብት መላሸቅ ባለሙያዎች ተንብየውት ከነበረው 3% ይበልጣል።
መስከረም አጋማሽ ላይ በመዲናዋ ጃካርታ በድጋሚ በከፊል የእንቅስቃሴ ገደብ ታውጇል። ኤኤንኬ ባንክ እንዳለው፤ የኢንዶኔዥያ ምጣኔ ሀብት እስከዛሬ ከታየው ዝቅተኛው ነጥብ ላይ ደርሷል።
የአገሪቱ መንግሥት ወረርሽኙ ካሳደረውን ተጽዕኖ በፍጥነት ለማገገም እና የአገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቋል።