አቶ ልደቱ ህክምና እንዲያገኙ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ

አቶ ልደቱ ህክምና እንዲያገኙ ፍርድ ቤት ዛሬ ትዕዛዝ መስጠቱን ተከትሎ ነገ ህክምና እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ገለጹ።
“ህመም እየተሰማቸው ስለሆነ ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ ህክምና እንዲያገኙ ትዕዛዝ እንዲሰጥልን” የሚል ማመልከቻ ማቅረባቸውን በዚሁ መሠረት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ በመስጠቱ ነገ ወደ ሐኪም ይሄዳሉ ሲሉ አቶ አዳነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ልደቱ ስላሉበት የጤና ሁኔታ ቢቢሲ ላቀረበላቸው ጥያቄም “በእውነት ምንም ሳልደብቅ መናገር የምፈልገው ነገር ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ የህመም ስሜት ይታይባቸዋል። ሰውነታቸው ትንሽም ቢሆን ቀነስ ብሏል። በእርሳቸው ህመም ሰው እንዲጨነቅ ስለማይፈልጉ በጣም ካልባሰባቸው በስተቀር ህመማቸውን እና ስቃያቸውን ለሰው መናገር አይፈልጉም።
"በዚህ ሳምንት በሦስቱ ቀናት ያየነው ነገር ግልጽ ህመም እየተሰማቸው እንደሆነ፤ በህይወታቸውም ላይ አደጋ እንዳይደርስ እየሰጉ እንደሚተኙ ነው። ከዚያ በፊት ህመም አይሰማኝም አታስቡ አትጨቁ ነበር የሚሉት” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
“ስለዚህ በተቻለ መጠን ነገ ህክምና የሚሄዱልን ከሆነ ቢያንስ የህክምናውን ውጤት ዶክተሩ እንዲጽፍልን እናደርግና እንደገና መልሰን ህይወታቸው አደጋ ውስጥ እንዳይወድቅ የሚደረገውን ጥረት አጠናክረን መቀጠል ነው” ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
ለህክምና ውጭ በነበሩበት ወቅት ሌላ ህመም እንዳለበቻው ተገልጾላቸው ቀዶ ጥገና አድረገው የስድስት ወር ቀጠሮ ተሰጥቷቸው እንደነበርም አቶ አዳነ አስታውሰዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ከዶክተሩ ጋር ሲጻጻፉ ቆይተው በዓመታቸው ሊሄዱ እንደነበር ገልጸው ሆኖም ለህክምና ወደ ውጭ ሊሄዱ ሁለት ቀን ሲቀራቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።
“ህክምናው በሃገር ውስጥ የሚገኝ አይደለም። የእሳቸው ህመም መሣሪያው ሃገር ውስጥ የለም። የሚታከሙበትን መሣሪያ እኔም ጠይቄዋለሁ። አሁን ዝም ብሎ ለቼካፕ ካልሆነ የሚሄደው ‘የእኔን [ህመም] ሊመረምር የሚችል መሣሪያ ሃገር ውስጥ የለም ነው’ ያለው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ አባል የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ከወራት በፊት በቁጥጥር ሥር ውለው አሁንም እሥር ቤት ይገኛሉ።














