ኮሮናቫይረስ፡ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ራሳቸውን ማግለላቸውን ገለጹ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊው ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም በቅርቡ ከእሳቸው ጋር ንክኪ የነበረው ግለሰብ በኮሮናቫይረስ መያዙ መረጋገጡን ተከትሎ ራሳቸውን አግልለው እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ዶክተር ቴድሮስ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት የበሽታው ምልክት እንደማይታይባቸው ገልጸዋል።

''በኮቪድ-19 መያዙ ከተረጋገጠ ግለሰብ ጋር ንክኪ እንዳለኝ ታውቋል። በጥሩ ጤንነት ላይ ነው የምገኘው፤ ምንም የቫይረሱን ምልክቶችም እያሳየሁ አይደለም። ነገር ግን በዓለም ጤና ድርጅት መመሪያዎች መሰረት ለሚቀጥሉት ቀናት ራሴን አግልዬ እቆያለሁ። ሥራዬንም ከቤቴ እሰራለሁ'' ሲሉ በትዊተር ገጻቸው በኩል አስታውቀዋል።

''እኔ እና የዓለም ጤና ድርጅት ባልደረቦቼ የሰዎችን ሕይወት ለማዳንና ተጋላጭ የሆኑትን ከቫይረሱ ለመከላከል አብረውን ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር ያለንን የትብብር ሥራ እናስቀጥላለን'' ሲሉም አክለዋል።

''ሁሉንም የጤና መመሪያዎች መከተል የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው'' ብለዋል የ55 ዓመቱ የቀድሞ የኢትዯጵያ የጤና ሚኒስትር።

''የኮቪድ-19 ስርጨት ሰንሰለትን መስበር የምንችለው በዚህ መንገድ ነው። ይህንን ካደረግንም ቫይረሱን እናሸንፈዋልን፤ የጤና ስርአታችንንም እንከላከለዋለን'' ብለዋል።

ዶክተር ቴድሮስ የዓለም ጤና ድርጅትን መምራት የቻሉ ብቸኛው አፍሪካዊ ናቸው።

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ሆነው ሲሾሙ በየዓመቱ ሚሊዮኖችን እየገደሉ ያሉ እንደ ወባ፣ ኩፍኝና ኤድስን እገታለሁ ሲሉ ነበር በወቅቱ ቃል የገቡት።

ምንም እንኳ መሥሪያ ቤታቸው እነዚህን በሽታዎች ለመግታት ቢታገልም፤ በሥልጣናቸው መባቻ ከባድ ፈተና ሆኖባቸው የነበረው ኮንጎ ውስጥ የተቀሰቀሰው ኢቦላ ነበር። አሁን ደግሞ ኮሮናቫይረስ።