የአይቮሪ ኮስት ተቃዋሚዎች ሰላማዊ ሽግግር እንዲካሄድ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ያሳለፍነው ቅዳሜ የተካሄደውን ምርጫ አንሳተፍም ያሉት የአይቮሪ ኮስት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ሰላማዊ ሽግግር ያስፈልጋል ማለታቸው ተሰምቷል።
ፓስካል አፊ ናጉሴን እና ሄነሪ ኮናን ቤይዴ እንዳሉት፤ ፕሬዘዳንት አላሳኔ ኦቱራ ለሦስተኛ ጊዜ ለምርጫ መቅረባቸው ሕገ ወጥ ነው። የፕሬዘዳንቱ ደጋፊዎች ግን ይህንን አይቀበሉም።
እአአ 2016 ላይ ሕገ መንግሥቱ እንደተለወጠና የፕሬዝዳንቱ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን እንደማይቆጠር ይናገራሉ። ዜጎች የሰጡት ድምጽ ገና እየተቆጠረ ነው።
ፕሬዘዳንቱ ነሐሴ ላይ ለሦስተኛ ጊዜ እንደሚወዳደሩ ይፋ ሲያደርጉ አለመረጋጋት ተክስቶ ነበር። 16 ሰዎችም ተገድለዋል። ቅዳሜ ምርጫው ሲካሄድ ደግሞ ቢያንስ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።
በርካታ የምርጫ ጣቢያዎች በተቃዋሚዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ተቃዋሚዎች መንገድ የዘጉባቸው ግዛቶችም ነበሩ። ተቃዋሚዎቹን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተተኩሷል። ዋነኛ የተቃዋሚ ፖርቲ መሪዎች ሕዝቡ “አምባገነናዊ አገዛዝን ይግታ” ሲሉም ተደምጠዋል።
ፓስካል አፊ ናጉሴን፤ “ፓርቲዎች እና ፖለቲከኞች ሰላማዊ ሽግግር ይሻሉ። የፕሬዘዳንቱ የሥልጣን ዘመን የሚያከትመው ጥቅምት 31 መሆኑን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማወቅ አለበት” ሲሉ ለሕዝቡ ተናግረዋል።
ሰላማዊ ሽግግር በማድረግ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ መካሄድ እንደሚገባውም ተቃዋሚው አክለዋል። ገለልተኛ የምርጫ ቡድን የሆነው ኢንዲጎ ኮትዲቯር ቢያንስ ሁለት አባላቱ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ቡድኑ እንደሚለው በምርጫው እለት 21 በመቶ የሚሆኑ ጣቢያዎች ዝግ ነበሩ።
የምርጫ ኮሚሽን በበኩሉ ከ22,381 ጣቢያዎች መካከል ዝግ የነበሩት 50 ብቻ ናቸው ብሏል። 35,000 የጸጥታ ኃይሎች የምርጫ ቁሳቁስ በማሰራጨት እና ሰላም በማስጠበቅ እንደተሳተፉ ተነግሯል።
ፕሬዘዳንቱ “የሰው ሕይወት እየጠፋበት ያለው ተቃውሞ መቆም አለበት። አይቮሪ ኮስት ሰላም ትሻለች” ሲሉ ለተቃዋሚዎች ተናግረዋል። በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት አንድ ፕሬዘዳንት ከሁለት ጊዜ በላይ መመረጥ አይችልም። ፕሬዘዳንቱም ይህንን መርህ አከብራለሁ ብለው ነበር።
ነገር ግን የገዢው ፓርቲ ፕሬዘዳንታዊ እጩ የነበሩት ጠቅላይ ሚንስትር አማዱ ጎን በልብ ድካም ሳቢያ ሲሞቱ፤ ፕሬዘዳንቱ በድጋሚ እንደሚወዳደሩ አስታወቁ። በአገሪቱ ዋነኛ ፖለቲከኞች መካከል ዓመታት የዘለቀ አለመግባባት ይስተዋላል።
እአአ 2010 ላይ የያኔው ፕሬዘዳንት ላውረንት ጋግቦ፤ ለፕሬዘዳንት አላሳኔ ኦቱራ እውቅና አልሰጥም ማለታቸውን ተከትሎ የእርስ በእርስ ግጭት ተከስቶ ነበር። በአምስት ወር ውስጥም ከ3,000 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።












