"በኬንያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ነው"

ታትሟል

በኬንያ ከባለፈው ወር ጀምሮ የሚመዘገበው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ "በአስደንጋጭ ሁኔታ" መጨመሩን የአለም ጤና ድርጅት አሳውቋል።

ድርጅቱ እንዳለው አገሪቷ 4 ሺህ 594 አዳዲስ ህሙማንን ባለፈው ሳምንት ያገኘች ሲሆን ይህም ከዚያ በፊት ከነበረው ሳምንት ጋር ሲወዳደር 51 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ብሏል።

"ከዚህ ቀደም ጣሪያ ላይ ደርሶ የነበረው ሐምሌ ወር ላይ ሲሆን በወቅቱም 4 ሺህ 700 የተመዘገበበት ወቅት ነበር። የአሁኑም ሁኔታ ከዚያ ብዙ የተለየ አይደለም። ሆኖም በአሁኑ ወቅት የሟቾች ቁጥር ዝቅተኛ በሚባል ሁኔታ 9 በመቶ ጭማሪ ነው ያሳየው" ብሏል የአለም ጤና ድርጅት

የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር ሙታይ ካግዌም አገሪቷ ወደ ሁለተኛ ዙር ወረርሽኝ ልታመራ ትችላለች በማለት አስጠንቅቀዋል።

በመስከረም አጋማሽ አገሪቷ ከምትመረምራቸው መከካል ከ5 በመቶ በታች የነበረው ቁጥር ባለፈው ሳምንት ወደ አስር በመቶዎቹ ኮሮናቫይረስ ይገኝባቸው ጀምሯል።

ይህም ከምርመራው ቁጥር ጋር የተያያዘ አይደለም ተብሏል።

አገሪቷ የኮሮናቫይረስን ለመግታት ጥላቸው የነበሩ መመሪያዎች ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል።

አገሪቷ መጠጥ ቤቶችን ከመዝጋት በተጨማሪ የአልኮል መጠጦች በሬስቶራንቶች እንዳይሸጡ ከልክላ ነበር።

በአሁኑ ወቅትም እግዱ ተነስቶ መጠጥ ቤቶች እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት እንዲሰሩ ተፈቅዶላቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የሰዓት እላፊ አዋጁም በተወሰነ መልኩ እንዲገፋ ተደርጓል።

ኬንያ በወረርሽኙ ምክንያት ዘግታቸው የነበሩ ትምህርት ቤቶቿንም በቅርቡ ከፍታለች።

በባለፈው ሳምንት ኬንያ የመዘገበችው ቁጥርም በአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛልም ተብሏል። ቁጥሩ ሞሮኮ፣ ቱኒዝያ፣ ግብፅ፣ ጂቡቲ፣ ሱዳንና ሶማሊያ አልተካተቱበትም ተብሏል።