የናይጄሪያን ተቃውሞ ለመቆጣጠር ፖሊስ በሙሉ ኃይሉ እንዲሰማራ ታዘዘ

ዘረፋ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በናይጄሪያ እየተስፋፋ የመጣውን ተቃውሞ ተከትሎ የአገሪቱ ፖሊስ አዛዥ ሁሉም የፖሊስ አባላት በፍጥነት ተደራጅተው እንዲሰማሩ ማዘዛቸው ተሰምቷል።

''ከፖሊስ ጭካኔ ጋር በተያያዘ ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ የነበሩ ሰልፈኞች ጉዳይ የህዝቡን ሰላም በሚያደፈርሱና አለመረጋጋትን በሚፈጥሩ ሰዎች ታግቷል'' ሲሉ ተደምጠዋል ኃላፊው ሞሀመድ አዳሙ።

ኃላፊው እንዳሉት እንዲህ አይነት ተግባር ከዚህ በኋላ ተቀባይነት አይኖረውም። አክለውም የፖሊስ አባላት በአገሪቱ እየተፈጸሙ ያሉ ግድያዎችን፣ ጭካኔዎችና ዝርፊያዎችን ለማስቆም ነው የተሰማሩት ብለዋል።

ፖሊሶች አንድን ሰው ሲገድሉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል መውጣቱን ተከትሎ ነው ከሳምንታት በፊት የተጀመረው ተቃውሞ የተቀጣጠለው።

እነዚህ ተቃውሞዎች በተለይም ዘረፋን ለማስቆም የተቋቋመውን ልዩ የፌደራል ፖሊስ ኃይል ወይም 'ሳርስ' ተብሎ የሚታወቀው ላይ ያነጣጠሩ ሲሆኑ፤ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን ማሰር፣ ማሰቃየትና ግድያም ይፈፅማል በሚልም ከፍተኛ ውግዘትም ቀርቦበታል።

ከፍተኛ ተቃውሞ የቀረበበት ሳርስ እንዲበተን ቢደረግም የሳርስ አባላት በሌሎች የፖሊስ ክፍሎች እየተዘዋወሩ እና እየተመደቡ ነው መባሉን ተከትሎ ነው እንደገና ተቃውሞቹ የቀጠሉት።

ሰልፈኞቹ እነዚህ የሳርስ አባላት ለፈፀሙት ወንጀል ህግ ፊት መቅረብ አለባቸው እያሉ ነው፤ እንዲሁም በአስተዳደሩ ላይ ማሻሻያም ያስፈልጋል ይላሉ።

ከሰሞኑ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት "ስር ነቀል" የፖሊስ ማሻሻያ እንደሚደረግና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል የተባሉትም የሳርስ አባላት ወደ ፍርድ ይቀርባሉ ብለው ነበር።

በሌጎስ በቅርብ ቀናት እየተካሄዱ ካሉ የተቃውሞ ሰልፎች ጋር በተያያዘ ሱቆች፣ የገበያ ማዕከላትላ መጋዘኖች እየተዘረፉ ነበር። የበርካቶችም ንብረት ጉዳት ደርሶበታል ተብሏል። በተጨማሪም አንዳንድ ህንጻዎች በእሳት እንዲጋዩ ተደርገዋል።

ቅዳሜ ዕለት ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቡኩሩ የሚገኙ የመንግስት መጋዘኖች ላይ ጥቃት በማድረስ ንብረት መዝረፋቸውም ተዘግቧል። መጋዘኖቹ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ለዜጎች ምግብ ለማከፋፈያነት የሚያገለግሉም ነበሩ ተብሏል።

ፕሬዝደንት ሞሀመዱ ቡሀሪ እስካሁን ቢያንስ 69 ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ ገልጸዋል።