ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስያ፡ ሁለቱ ቢሊየነሮች እጅግ ቅንጡ መኖርያ ቤት ተሻሻጡ
ሁለቱ ቢሊየነሮች በሲንጋፖር እጅግ ቅንጡ የፎቅ ላይ መኖርያ ቤት ተሻሻጡ፡፡
እንግሊዛዊው ሰር ጄምስ ዳይሰን በሲንጋፖር የሚገኘውን የፎቅ ማማ ላይ ቅንጡ ቤቱን (ፔንትሀውስ) ሊሸጠው መሆኑ ተሰምቷል፡፡
ሰር ዳይሰን ቤቱን የሚሸጠው በ47 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህም ወደ 1 ቢሊዮን 800 ሚሊዮን ብር ይጠጋል፡፡
ገዢው ቢሊየነር ደግሞ መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገ ትውልድ ኢንዶኔዢያዊ ነው፡፡
ሰር ዳይሰን ይህንን ቤት እየሸጠው የሚገኘው ባለፈው ዓመት ከገዛበት ዋጋ በታች ነው፡፡
ይህ የፎቅ ማማ ላይ ቅንጡ ቤት (ፔንትሃውስ) ሰር ዳይሰን ሲገዛው 73.8 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ተዘግቦ ነበር፡፡
በተጨማሪም ሰር ዳይሰን ቤቱን ሲገዛው ዝነኛውን የዳይሰን ኩባንያ ዋና ጽሕፈት ቤቱን ሲንጋፖር ለመውሰድ መወሰኑን ተናግሮ ነበር፡፡
ኢንጂነሩ ሰር ጀምስ ዳይሰን የዳይሰን ኩባንያ መሥራችና ባለቤት ሲሆን ኩባንያው በዓለም ላይ የምንጣፍ ማጽጃ (ቫኩዩም ክሊነር) እና የጸጉር ማድረቂያ ቁሳቁሶችንና እንዲሁም ሌሎች ከጽዳት ጋር የሚያያዙ የቤት ቁሳቁሶችን በማምረት ገናና ስም አለው፡፡
ሰር ዳይሰን በሲንጋፖር የኤሌክትሪክ መኪና ፋብሪካ ሊገዛ እንደሆነም ተዘግቦ ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን ከገበያ አዋጪነት ጋር በተያያዘ ውሳኔውን ሰርዞታል፡፡
ሰር ጀምስ በሰንደይ ታይምስ የዚህ ዓመት ቁጥር አንድ የታላቋ ብሪታኒያ ቢሊየነር ሆኗል፡፡ ጠቅላላ ሀብቱም ወደ 16 ቢሊዮን ዶላር ተጠግቷል፡፡
እንግሊዝ ከአውሮጳ ኅብረት እንድትፋታ ከፍተኛ ፍላጎት ያለው ሰር ዳይሰን ፋብሪካውን ወደ ሲንጋፖር ለማዘዋወር በመወሰኑ ሲተችበት ነበር፡፡
በሲንጋፖር ትልቁና እጅግ ግዙፍ የተባለው ይህ የፎቅ ማማ መኖርያ ቤት በጋውኮ ታወር 64ኛ ፎቅ ላይ የሚገኝ ነው፡፡
ቤቱ የዚህን የጎውኮ ታወር የላይኞቹን 3 ወለሎች የያዘና እጅግ ግዙፍ የሚባል ነው፡፡ 5 ሰፋፊ መኝታ ቤቶች ሁሉም የሲንጋፖርን ሰማይ ጠቀስ ፎቶች ቁልቁል ለማየት የሚያስችሉ ናቸው፡፡
በሲንጋፖር ፎቅ ላይ ከተገነቡ ቤቶች ሰፊው ይህ የሰር ዳይሰን ቤት ነው፡፡
የቤቱ ገዢ ትውልደ ኢንዱኔዢጠያዊውና የኮምፒውተር ሶፍትዌር አምራች የኤስኤችአይ ኢንተርናሽናል መሥራች ሊዮ ካጉዋን ነው፡፡
እንግዛዊው ቁጥር አንድ ቢሊየነር ሰር ዳይሰን በሲንጋፖር ሌላ 50 ሚሊዮን የሲንጋፖር ዶላር የሚያወጣ ቪላን በባለቤትነት ያስተዳድራል፡፡