የአል-ሸባብ ተቀጣጣይ ፈንጅ መስሪያ ግብዓት ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሶማሊያ ደህንነት ቢሮ በአል-ሸባብ አማካኝነት በሕገ ወጥ ወደ አገር ውስጥ የገባ 79 ቶን ሰልፈሪክ አሲድ ያዝኩ አለ።
ብሔራዊ የደህንት ኤጀንሲ እንዳለው ከሆነ 79ሺህ ኪሎ ግራም የሚመዝነው ሰልፈሪክ አሲድ ወደ ሶማሊያ የገባው አል-ሸባብ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን እንዲያመርትበት ነበር።
"79 ቶን ሰልፈሪክ አሲድ እና ሰልፈሪክ አሲዱን ወደ አገር ውስጥ ያስገቡ በርካታ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውለናል" ብሏል ኤጀንሲው በትዊተር ገጹ ላይ።
ኤጀንሲው ጨምሮ እንዳስታወቀው ግለሰቦቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰልፈሪክ አሲዱን አል-ሸባብ ወደሚቆጣጠረው ስፍራ እያጓጓዙ ሳሉ ነው።
ምንም እንኳ ሰልፈሪክ አሲዱ የተያዘበትም ቀን ይሁን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉበት ቀን ይፋ ባይደረግም ተጠርጣሪዎቹ ግን ፍርድ ቤት መቅረባቸው ተመልክቷል።
ኤጀንሲው ይህን ያክል መጠን ያለው ሰልፈሪክ አሲድ መያዙን ያሰማው በሶማሊያ መዲና በሽብር ጥቃት ከ600 በላይ ሰዎች የተገደሉበት ሶስተኛ ዓመት እየታሰበ በሚገኝበት ዕለት ነው።
የዛሬ ሶስት ዓመት እአአ 2017 ላይ ለተፈጸመው ጥቃት አል-ሸባብ ኃላፊነቱን ባይወስድም በሞቃዲሹ ተመሳሳይ ጥቃቶችን ሲፈጽም ቆይቷል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ የተባበሩት መንግሥት የጸጥታው ምክር ቤት አል-ሸባብ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን ለመስራት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ከውጪ ወደ ሶማሊያ ደብቆ የማስገባት አቅም እንዳለው አስታውቆ ነበር።
መቀመጫውን ሶማሊያ ያደረገው ጽንፈኛው ቡድን አል-ሸባብ በሶማሊያ እና ኬንያ ጭምሮ በመስራቅ አፍሪቃ አገራት በርካታ ሰዎች የተገደሉበት ጥቃቶችን ሰንዝሯል።













