ኖርዌይ በምክር ቤቷ ለተፈጸመው የሳይበር ጥቃት ሩሲያን ተጠያቂ አደረገች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኖርዌይ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር በፓርላማዋ የኢሜይል ሥርዓት ላይ ለደረሰው የሳይበር ጥቃት ሩስያን ተጠያቂ አደረገች።
የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚንሰትር አይን ኤሪክስን ሶሬድ የአገራችን ከፍተኛ የዲሞክራሲ ተቋም ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው በማለት የጥቃቱን ክብደት አመልክተዋል።
"መንግሥት አሁን ባለው መረጃ መሠረት ከጥቃቱ ጀርባ ሩሲያ ስለመኖሯ ደርሰንበታል" ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ። ሚንስትሯ ጥቃቱ በሩሲያ ስለመፈጸሙ የሚያመላክቱ ማስረጃዎችን ግን ይፋ ከማድረግ ተቆጥበዋል።
ሞስኮ በበኩሏ የኖርዌ መንግሥት ወቀሳን አጣጥላለች። በኦስሎ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ለዚህ ወቀሳ የቀረበ ምንም አይነት ማስረጃ የለም ብሏል።
ኤምባሲው በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የሳይበር ጥቃቶች በሩሲያ ላይ እንደሚፈጸሙ አስታውሶ በኖርዌይ ለተፈጸመው ጥቃት ሩሲያን ተጠያቂ ማድረግ አግባብ አይደለም ብሏል።
የኖርዌ ባለስልጣናት እንዳሉት ከሆነ በተቃጣው የሳይበር ጥቃት የበርካታ ባለስልጣናት የኢሜይል አድራሻዎች ተጋላጭ ሆነው ነበር።
በአንዳንድ የኢሜይል አድራሻዎች ውስጥ የነበሩ መረጃዎችም በመረጃ በርባሪዎቹ መገልበጣቸውን አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ በዚህ የሳይበር ጥቃት የደረሰው ሙሉ የጉዳት መጠን አልተገለጸም።
ይህ የኖርዌይ ወቀሳ የተሰማው የሩሲያ እና ኖርዌይ ግንኙነት ከመቼውም በላይ በሻከረበት ወቅት ነው።
ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ኖርዌይ ሲሰልል ነበር ያለችውን የሩሲያ ዲፕሎማት ከአገሯ አባራለች። በምላሹም በቀናት ልዩነት ሩሲያ ከሞስኮ የኖርዌይ ዲፕሎማትን ከአገሯ አስወጥታለች።
እአአ 2018 ላይ ደግሞ ኖርዌይ ስለ ፓርላማ ኔትዎርክ መረጃ ሲሰበስብ ደርሼበታለሁ ያለችውን የሩሲያ ዜጋ በቁጥጥር ሥር አውላ ነበር። ግለሰቡ ዘግይቶም ቢሆን ከእስር ተለቋል።
ከወራት በፊት ደግሞ የኖርዌይ ደኅንነት መስሪያ ቤት ሩሲያ የኖርዌይ ሕዝብ በመንግሥቱ፣ በመገናኛ ብዙሃን እና የምርጫ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲያጣ ለማድረግ የሩሲያ መንግሥት እያሴረ ነው ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።
ሁለቱ አገራት የአርክቲክ ድንበርን የሚጋሩ ሲሆን ኖርዌይ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት- ኔቶ አባል አገር ናት።















