በኮንጎ ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎች በምግብ እጥረት እየሞቱ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኦፍ ኮንጎ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ታራሚዎች በምግብ እጥረት ሳቢያ እየሞቱ መሆኑ ተነገረ።
በቅርቡም የ18 ዓመቱ ወጣት ሙኖ ሌምቢሳ ቡኒዓ ሴንተራል ፕሪዝን ተብሎ በሚጠራው ማረሚያ ቤት ውስጥ ለመሞቱ አንዱ ምክንያት የምግብ እጥረት መሆኑን የማረሚያ ቤቱ ዳይሬክተር ለሬውተርስ ተናግረዋል።
ወጣቱ በዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኦፍ ኮንጎ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ በሚገኘው ቡኒዓ ማረሚያ ቤት ውስጥ በምግብ እጥረት ምክንያት ከሚሞቱ በርካታ ታራሚዎች መካከል አንዱ ነው።
የማረሚያ ቤቱ ዳይሬክተር ወጣቱ ከውጪ ምግብ እያመጡ የሚጠይቁት ሰዎች ስላልነበሩት ለመሞቱ ምክንያት አንዱ የምግብ እጥረት ሆኗል ብለዋል። ባለፉት 10 ወራት ብቻ ቡኒዓ ተብሎ በሚጠራው ማረሚያ ቤት ብቻ ከ50 በላይ ታራሚዎች በምግብ እጥረት ምክንያት መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታትን ዋቢ በማድረግ ሬውተርስ ዘግቧል።
በዲሞክራቲክ ኮንጎ የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ከአቅማቸው በላይ ታሳሪዎችን በመያዝ ከመጨናነቃቸውም በላይ ለታሳሪዎች የሚሆን በቂ ምግብ አያቀርቡም። በቅርቡ በማረሚያ ቤት ሕይወቱ ያለፈው ሌምቢሳ በአስገድዶ መድፈር ጥፋተኛ ተብሎ አንድ ዓመት ተፈርዶበት ነበር።
“የተላለፈበት ፍርድ እጅጉን አበሳጭቶታል። በዚህም ምክንያት ክብደቱ በፍጥነት መቀነስ ጀመረ” በማለት የእስር ቤት ጓደኛው ዴቪድ ኢሎፓ ለሬውተርስ ተናግሯል። “ጭንቀቱ እና ረሃቡ እጅጉን ጎድተውት ነበር” ሲል ሌላኛው ታራሚ ዴትሱቪ ኤሊ ይናገራል።
የቡኒዓ ሴንተራል እስር ቤት ዳይሬክተር ካሚሌ ናዞንዚ ለወጣቱ ሞት አንዱ ምክንያት የምግብ እጥረት መሆኑን አምነዋል። “የተላለፈበት ፍርድ ብቻ አይደለም የጎዳው። የምግብ እጥረት ለመሞቱ አንዱ ምክንያት ነው። ከውጪ ጠያቂ የሌላቸው እስረኞች ማረሚያ ቤቱ የሚያቀርብላቸውን ምግብ ብቻ ነው የሚያገኙት” ሲሉ ይናገራሉ።
በእስር ቤቱ የሚገኙት ታራሚዎች እንደሚሉት ምግብ ይዘው መጥተው የሚጠይቁ ወዳጅ ዘመዶች የሌሉት ታራሚ በቀን ግፋ ቢል ሊመገብ የሚችለው አንዴ ብቻ ነው።
250 ታሳሪዎችን ለመያዝ የተገነባው ይህ ማረሚያ ቤቶች በአሁኑ ወቅት ከ1ሺህ 250 በላይ ታሳሪዎች ይገኙበታል። የኮንጎ የሰብዓዊ መብቶች ሚንስትር አንድሬ ላይት፤ “የእስር ቤቶችን አስተዳደር ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት መደረግ አለበት። ይህ የማይካድ ሃቅ ነው” ይላሉ።
በኮንጎ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የምግብ እጥረት የተለመደ ክስተት መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ የሂዩማን ራይትስ ዎች አጥኚው ቶማስ ፌሰይ ናቸው።
“ቤተ-ክርስቲያናት፣ በጎ አድራጊ ድርጅቶች እና ፍቃደኛ ግለቦች ጥረት ባይታከልበት ኖሮ በኮንጎ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ታራሚዎች ምግብ መመገብ አይችሉም ነበር” ይላሉ።












