ዘረኛ ነው የተባለው ምስል ዓለም አቀፍ ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, @BRYANBOY
ኮሮረናቫይረስ በመላው ዓለም መሰራጨቱን ተከትሎ ከእሲያ አገራት የሚመጡ ሰዎች መግለል እያጋጠማቸው ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ገልጸዋል፤ እየገለጹም ነው።
ነገር ግን የፋሽን ኢንደስትሪው ተጽህኖ ፈጣሪው 'ብራያንቦይ' በስዊድን አንድ ምግብ ቤት ውስጥ ተለጥፈው የተመለከታቸው 'ዘረኛ' ምስሎች በእጅጉ እንዳስደነገጡት ይገልጻል።
''ምግብ ቤት ውስጥ ገብተን የምንመገበውን ነገር ካዘዝን በኋላ ነበር ግድግዳው ላይ የተለጠፈውን ምስል የተመለከትነው። የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ዢን ፒንግ ፊታቸው በጣም ቢጫ ተደርጎና የሌሊት ወፍ ጆሮ ተጨምሮላቸው፤ የሌሊት ወፉ ሰው የሚል ጽሁፍም ከስር ተመለከትኩ'' ብሏል።
ምግብ ቤቱ በግድግዳው ላይ የነበረውን ምስል አሁን አውርዶታል።
በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም የሚገኘው ይህ ምግብ ቤት በግድግዳው ላይ ተለጥፎ የነበረውን ምስል በርካቶች ዘረኛ እንደሆነ በማሰባቸው እንዳወረደውና ዓላማቸው ግን ከረዘኝነት ጋር የተያያዘ እንዳልነበር አስታውቋል።
አክሎም በምስሎቹ ስሜቱ የተጎዳው ካለ ይቅርታ እጠይቃለሁ ብሏል ድርጅቱ።
የግድግዳ ላይ ስዕሎቹን የሰራው አርቲስትን የሚወክለው ድርጅት በበኩሉ ስዕሎቹ ላደረሱት ጉዳት ይቅርታ ጠይቃለሁ ያለ ሲሆን ለስዕሎቹ ግን ይቅርታ አልጠይቅም ብሏል።
''በስራዬ የማልተማመን ቢሆን ኖሮ መጀመሪያውኑ ስዕሉን አልሰራውም ነበር። ነገር ግን በሰራሁት ስራ አላፍርም። ነገር ግን የሰዎችን ስሜትም መጉዳት አልፈልግም። ስዕሉን ስሰራውም ሀሳቤ እሱ አልነበረም''
የማህበራዊ ሚዲያ ተጽህኖ ፈጣሪው 'ብራያንቦይ' በስቶክሆልም ከጓደኛው ጋር ምግብ ለመመገብ በገቡቡት በተመለከቱት ነገር በእጅጉ መደንገጣቸውን ገልጿል።
''ኮቪድ-19 ከተከሰተበት ዕለት አንስቶ እኔ እና አብዛኛው ከእሲያ አገራት የመጣን ሰዎች በርካታ ዘረኝነትና ጥላቻ ደርሶብናል። በአካልም ሆነ በበይነ መረብ አማካይነት። እንዲህ በግልጽ ስመለከተው ደግሞ በጣም ነበር የተሰማኝ''
አክሎም ምንም እንኳን ምግብ አዝዘው ቢሆንም የተቀመጡት በተመለከቱት ነገር በእጅጉ በማዘናቸው ጥለው እንደወጡ ገልጿል።
ግድግዳው ላይ የተሰቀለው የዢ ዢን ፒንግ ስዕል ኮሮረናቫይረስ የመጣው ከሌሊት ወፎች ነው የሚለውን ሀሳብ ለመደገፍ የታሰበ ሲሆን በምግብ ቤቱ ውስጥ ለበርካታ ሳምንታት ተሰቅሎ ቆይቷል።
የኮሮረናቫይረስ ወረርሽን ከተከሰተ ወዲህ በርካቶች የዘረኝነትና ጥላቻ ሰላባ ሆነዋል። በተለይ ደግሞ ቻይናውያን ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች በርካታ ነበሩ።
ለንደን ውስጥ ከሲንጋፖር የመጣ አንድ ተማሪ በቡድን የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ድብደባ ፈጽመውበት ነበር። በወቅቱም ''የአንተን ኮሮናቫይረስ አገራችን ውስጥ ማየት አንፈልግም'' በማለት ድብደባውን እንደፈጸሙበት ገልጿል።
ስዕሉን የሰራው ግለሰብ በኢንስታግራም ገጹ ባስተላለፈው መልዕክት ስራው ምንም አይነት የዘረኝነት ሀሳብ እንደሌለውና የተለያዩ የዓለም መሪዎች ላይ እንደሚቀለደው ሁሉ በቻይናው መሪ ላይም ለማሾፍ የተደረገ ሙከራ ነበር ብሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ ዘረኝነት እንዳይሰፋፋ አስጠንቅቆ ነበር። ''ይህ ወረርሽኝ የዉሀን ቫይረስ፣ የቻይና ቫይረስ አልያም የእሲያ ቫይረስ አይደለም" ብሎ ነበር በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት።












