ስፖርት ፡ ሳዑዲ አረቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሴቶች የጎልፍ ውድድር ልታዘጋጅ ነው

የፎቶው ባለመብት, LADIES EUROPEAN TOUR
ሳዑዲ አረቢያ በመጪው ኅዳር ወር ከ 'አውሮፓ ሌዲስቱር ኤቨንትስ' ጋር በመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የሴቶች የጎልፍ ውድድር ልታዘጋጅ መሆኑ ተገለፀ።
በዚህ ዝግጅት ሁለት ውድድሮችን ለማካሄድም ታቅዷል።
ሁለቱም ውድድሮች በሮያል ግሪን ጎልፍ ክለብ እንደሚካሄዱም ተገልጿል። ሮያል ግሪን ጎልፍ ከጂዳ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ቦታ ሲሆን በመኪና 2 ሰዓት ያስጉዛል።
ይህ ውድድር መጋቢት ወር ላይ ይካሄዳል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ግን ተሰርዟል።
የአውሮፓ ሌዲስ ቱር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሌክሳንድራ አርማስ "በሳዑዲ አረቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው ታሪካዊ የሴቶች የጎልፍ ውድድር አካል በመሆናችን ደስ ብሎናል" ብለዋል።
ለጎልፍ ውድድር አስቸጋሪ በሆነው በዚህ ዓመትም ሁለት ውድድሮችን ለማካሄድ በመፍቀዳቸው አመስግነዋል ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ።
በዚህ ዝግጅት ለአንድ ውድድር ብቻ 1 ሚሊየን ዶላር ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን፤ ዝግጅቱን ለማካሄድ ደግሞ ተጨማሪ 637 ሺህ ዶላር ተይዟል።
በውድድሩ ልምድ ያላቸው ተወዳዳሪዎች ከአዳዲሶቹ ጋር በአዲስ አጨዋወት ይጣመራሉ ተብሏል።
ሁለቱም ውድድሮች ደኅንነታቸው በተጠበቁና ለበሽታው በማያጋልጥ ሁኔታ እንደሚካሄዱም ተገልጿል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በስዊዝ የሴቶች የጎልፍ ውድድር የመጀመሪያ ማዕረጓን የተቀበለችው የዌልሷ ኤሚ ቦልደን በበኩሏ "የሴቶች የጎልፍ ውድድር ለማካሄድ እንዲህ ዓይነት ቁርጠኝነት መኖሩ በጣም አስደናቂ ነው" ብላለች።
በአውሮፓ ሌዲስ ቱር ምርጥ የእንግሊዝ ተጨዋች በመሆን ያጠናቀቀችው የኢንግላንዷ ሜጋን ማክላረን፤ ውድድሩን ለማካሄድ ላሳለፍነው መጋቢት ወር ፕሮግራም ሲያዝ 'ስፖርትን ስም ለማደስ መጠቀም' በሚል ምክንያት ከውድድሩ ራሷን ለማግለል ወስና ነበር።
ሳዑዲ አረቢያ እንደዚህ ዓይነት ውድድሮችን በግዛቷ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን አጀንዳ ለማስለወጥ ትጠቀምበታለች የሚል ክስ ይቀርብባታል።
ሆኖም የቦክስ ውድድር፣ የሞተር እና የጎልፍ እንዲሁም ከሌሎች ውድድሮች ጀርባ ያሉ ሰዎች "ውድድሮቹ ሰዎች ንቁ እንዲሆኑ ለማድረግ የታቀደው ፕሮግራም አካል ናቸው" ሲሉ ለቢቢሲ ስፖርት ተናግረዋል።












