ኮሮናቫይረስ፡ በዩናይትድ ኪንግደም 40 ዩኒቨርስቲዎች በኮቪድ-19 የተያዙ ተማሪዎች ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኙ 40 ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ኮሮናቫይረስ የተያዙ ተማሪዎች መገኘታቸው ተገለፀ። በዚህም የተነሳ አዲሱ የትምህርት ዘመን ሲጀመር በሺህዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ራሳቸውን አግልለው ይቆያሉ ተብሏል።
ከዚህም በኋላ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚታየው የኮሮናቫይረስ ስርጭት ይጨምራል ተብሎ ተሰግተወል።
የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ከቤታቸው ርቀው ለመሄድ ስጋት ገብቷቸው የነበረ ቢሆንም አሁን ግን በዩኒቨርስቲዎቹ ውስጥ በተከሰተው ወረርሽኝ የተነሳ ወደ ቤታቸው የመመለስ ስጋት ገብቷቸዋል።
በቅርቡ ዩኒቨርስቲ ኦፍ አብሪስቲዊዝ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚል የገጽ ለገጽ ትምህርትን አስቀርቷል።
ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ተማሪዎች ለገና እረፍት ወደ ቤታቸው መሄድ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ስኮትላንድ ውስጥ ተማሪዎች ለገና እረፍት ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑም ተገልጿል።
ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን ከመጀመራቸው በፊት የገጽ ለገጽ ትምህርት እንደሚኖር ተነግሯቸው የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ግን በወረርሽኙ ምክንያት ተቋማት ትምህርት በኢንተርኔት አማካይነት ወደ መስጠት ማዘንበላቸው ተሰምቷል።
በማንችስተር ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ ለቀጣዩቹ 14 ቀናት የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች በኢንተርኔት በኩል እንደሚማሩ ተገልጿል።
ዩኒቨርስቲው 127 ተማሪዎች የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጎላቸው ቫይረሱ እንዳለባቸው ሲረጋገጥ 1700 ተማሪዎች ደግሞ ለሁለት ሳምንት ራሳቸውን አግልለው እንዲቀመጡ ተደርጓል።
በተመሳሳይ ግላስኮ ዩኒቨርስቲ 172 ተማሪዎች ኮሮናቫይረስ ሲገኝባቸው 600 ተማሪዎች ራሳቸውን አግልለው እንዲቀመጡ ተወስኗል።
ኩዊንስ ዩኒቨርስቲ ቤልፋስት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች የኮሮናቫይረስ መያዛቸው በመረጋጋጡ የተወሰኑ ተማሪዎች ራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩ ተደርጓል።
በተጨማሪም ዩኒቨርስቲ ኦፍ ኤክስተር እንዲሁ ተመሳሳይ ርምጃ መወሰዱ ተሰምቷል።
በርካታ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎቻቸውን ቅይጥ በሆነ ስልት እንደሚያስተምሩ ታውቋል። ይህም በኢንተርኔትና በገጽ ለገጽ የሚሰጥ ትምህረትን ጎን ለጎን መስጠትን ያካትታል ተብሏል።
ተቋማቱ ትምህርት በገጽ ለገጽ እንሰጣለን ብለው ወደ ኢንተርኔት በመግባታቸው ገንዘባችንን ይመልሱልን የሚሉ ተማሪዎች ቁጥር ጨምሯል።














