ኮሮናቫይረስ ፡ ኮቪድ-19ን ለመዋጋት የቻይና የሕክምና ቡድን ዚምባብዌ መግባቱ ተገለፀ

የቻይና ሕክምና ቡድን በዚምቧብዌ

የፎቶው ባለመብት, Chinese embassy in Zimbabwe

ታትሟል

ዚምባብዌ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመዋጋት የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ 10 አባላት ያሉት የቻይና የሕክምና ቡድን ወደ አገሪቱ መግባታቸው ተገለፀ።

ዶክተሮቹ በፓሬንትዋ ግሩፕ ሆስፒታሎች ለመጪዎቹ 12 ወራት እንደሚቆዩ መንግሥታዊው ሄራልድ ጋዜጣ ዘግቧል።

የቡድኑ መሪ ሆኑት ዶክተር ሉኦ ዌጊያንግ ዶክተሮቹ የቻይናን ባህላዊ መድኃኒትም እንደሚያስተዋውቁ መናገራቸውን ጋዜጣው ጠቅሷል።

የቻይና ኤምባሲም 18 አባላት ያሉት የሕክምና ቡድን አባላት ዛሬ ዚምባብዌ መድረሱን ገልጾ፤ የአተነፋፈስ ሳይንስ፣ የማህፀንና ፅንስ፣ የቀዶ ሕክምና፣ የነርቭ፣ የጡንቻና የአጥንት እንዲሁም የቻይና ባሕላዊ መድኃኒት ባለሙያዎችን ጨምሮ፤ የሕክምና ቡድኑ አባላት በዚምባብዌና በቻይና መካከል ያለውን የጤና ትብብር በማጠናከር እንደሚሰሩ በትዊተር ገፁ ላይ አስፍሯል።

ዚምባብዌ ላለፉት ስድስት ወራት ተዘግተው የቆዩትን ትምህርት ቤቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የከፈተች ሲሆን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው።

ይሁን እንጂ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ለደኅንነታቸው በመስጋት የሁለት መምህራን ሕብረት አባላት አድማ ላይ ናቸው።

መንግሥት ተማሪዎች በትምህርት ቤት ደኅንነታቸው አንደሚጠበቅ ቢናገርም፤ የሕብረቱ ተወካይ ኦበርት ማሳራውሬ ተማሪዎች ቢመለሱም በአብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዳማይሰጥ ለቢቢሲ ኒውስደይ ተናግረዋል።

እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ በዚምባብዌ እስካሁን 7 ሺህ 812 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 227 ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት አሁንም እየጨመረ ሲሆን በተለይ ክፉኛ በቫይረሱ በተመቱት የአውሮፓ አገራት ወረርሽኙ በአሳሳቢ ሁኔታ እያገረሸ መሆኑ ተነግሯል።

ኮሮና
Banner