ለ2500 ዓመታት ተቀብረው የነበሩ ሬሳ ሳጥኖች ተገኙ

የሬሳ ሳጥኖች

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

ለ2500 ዓመታት ተቀብረው የቆዩ ከድንጋይ የተሠሩ ሬሳ ሳጥኖች በግብፅ ተገኙ።

27 የአስክሬን ማቆያዎች የተገኙት ሳቅራ በተባለ ከካይሮ በስተደቡብ ባለ አካባቢ ነው።

በዚህ ወር መባቻ 13 ሬሳ ሳጥኖች ተገኝተው ነበር። አሁን ደግሞ 14 ተጨማሪ ተገኝቷል። ግኝቱ ከእስከዛሬው የላቀ ነው ተብሏል።

በእንጨት የተሠሩና በተለያዩ ቀለማት የተዋቡ ሬሳ ሳጥኖች እንዲሁም ሌሎችም ቁሳ ቁሶችም ተገኝተዋል።

ሳቅራ ከ3,000 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ መካነ መቃብር ነው። የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በቅርስነት መዝግቦታል።

የግብፅ የጥንታዊ ቅርሶች ሚንስትር “እነዚህ ሬሳ ሳጥኖች ከተቀበሩ በኋላ እንዳልተከፈቱ የሚያሳይ መረጃ አግኝተናል” ብሏል።

ግኝቱ ይፋ የተደረገው ሚንስትሩ ካሊድ አልአናኒ ቦታው ላይ ተገኝተው ከጎበኙ በኋላ ነው። በቁፋሮው የተሳተፉ ባለሙያዎችንም አመስግነዋል።

ባለሙያዎቹ ሬሳ ሳጥኖቹን ያገኙት 11 ሜትር ቆፍረው ነበር። ስለ ሬሳ ሳጥኖቹ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ቁፋሮው ቀጥሏል።

ከወራት በፊት አስክሬናቸው የደረቀ እንስሳት ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ እይታ ቀርበው ነበር። እንስሳቱ የተገኙት ከሁለት ዓመት በፊት በሳቅራ ፒራሚድ አቅራቢያ ነው።

አስክሬናቸው የደረቀ ድመቶች፣ አዞዎች፣ ኮብራ እባቦች እና ወፎችም ተገኝተዋል።

ሳቅራ የጥንታዊ ግብፅ መዲና ለነበረችው ሜምፌስ የመካነ መቃብር ሰፍራ ነበረች። በእንደዚህ አይነት ሥፍራዎች የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶችን ግብፅ በስፋት ማስተዋወቁን ቀጥላለች።