የፓኪስታን ፖሊስ የተደፈረች ሴትን መውቀሱ ቁጣን ቀሰቀሰ

ፓኪስታን

የፎቶው ባለመብት, FAROOQ NAEEM

ታትሟል

ፓኪስታን ውስጥ ሴቶች እንዳያመሹ፣ ካመሹም ከወንዶች ጋር እንዲሆኑ በቤተሰቦቻቸው ይመከራሉ።

ሴቶች ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ወንዶችን ተከታትለው እንዲይዙ የተመደቡ አንድ ከፍተኛ የፖሊስ ኃላፊ፤ ሴቶች ምሽት ላይ ብቻቸውን በመሆናቸው ተጠያቂ ናቸው ማለታቸው ቁጣ ቀስቅሷል።

ተጎጂዎችን የሚወቅሰውን አስተያየት በርካቶች እየተቹት ነው።

የሴቶች መብት ተሟጋች ቡድን አባሏ ሞኒዛ አህመድ “ተጎጂዎችን መውቀስ በማኅበረሰቡ ዘንድ የቆየ አመለካከት ነው። ፖሊሱ በሰጡት አስተያየት ተቃውሞ መነሳቱ ሕብረተሰቡ ሴቶችን እየሰማ መሆኑ ማሳያ ነው” ብላለች።

የተፈጠረው ምንድን ነው?

መስከረም 9 ከሰዓት ላይ አንዲት ሴት ነዳጅ ሲያልቅባት ወደ ዘመዶቿ ደወለች። ሁለት ልጆቿ አብረዋት ነበሩ።

ዘመዶቿ ወደ ቀለበት መንገዱ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እንድትደውል ይነግሯታል።

ፖሊሶች እንዳሉት፤ በ30ዎቹ እድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሁለት ወንዶች መኪናዋን ሰብረው ገብተው ጌጣ ጌጥ ዘርፈው በልጆቿ ፊት አስገድደው ደፍረዋታል። ከአካባቢውም ተሰውረዋል።

ድንጋጤው አሁንም እንዳለቀቃት ፖሊሶች ይናገራሉ።

ይህን ተከትሎ የፖሊስ ኃላፊ ዑመር ሼክ፤ ለደረሰባት ጥቃት በከፊል ተጠያቂ ናት ብለው ለመገናኛ ብዙሀን ተናግረዋል።

ሰው በሚበዛበት መንገድ መንዳት ነበረባት፣ ያላትን ነዳጅ መጠንም ማየት ነበረባት ሲሉ ተጎጂዋን መልሰው ተጠያቂ አድርገዋል።

ንግግራቸው ከሁሉም አቅጣጫ አስወቅሷቸዋል።

የሰብአዊ መብት ሚንስትር ሸሪን ማርዚ “የተደፈረች ሴትን ይህን ብታደርግ፣ ያን ባታደርግ ብሎ መውቀስ ተቀባይነት የለውም። ምንም ነገር ለመደፈር ምክንያት ሊሆን አይችልም” ብለው ትዊተር ላይ ጽፈዋል።

የመብት ተሟጋቿ ሞኒዛ “ሴቶች በመደፈራቸው የሚወቀሱበትን፣ በምሽት መውጣት የሚከለከሉበትን አባታዊ አመለካከት እንታገላለን” ትላለች።

ለውጥ ፈላጊ ሴቶች

የፖሊስ ኃላፊው ይቅርታ ቢጠይቁም ቁጣው አልረገበም።

የመብት ተሟጋቾች፣ ምሁራን እና ሌሎችም በጋራ ንግግሩን መኮነናቸው እንዳስደሰታቸው የሕግ አማካሪው ሪማ ዑመር ተናግረዋል።

በዋና ዋና ከተሞች ተቃውሞ እየተካሄደ ነው። የፖሊስ፣ የህክምና፣ የፍርድ ቤትና የማረሚያ ቤት መዋቅር ላይ ማሻሻያ እንዲደረግም ተጠይቋል።

በእርግጥ ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶች ይህ ተጨባጭ ለውጥ ላያመጣ ይችላል። ፓኪስታን ውስጥ የመድፈር ክስ ተመስርቶ እምብዛም ፍትህ አይገኝም።

ሚንስትር ፋውድ ቻውድሪ እንደሚሉት፤ በየዓመቱ 5,000 የአስገድዶ መድፈር ሪፖርቶች ይደርሳሉ። የፍርድ ውሳኔ የሚሰጠው በአምስት በመቶው ላይ ብቻ ነው።

ሴቶች የፖሊስና የማኅበረሰቡን ማንጓጠጥ በመፍራት መደፈራቸውን አይናገሩም።

ጠበቃና የማኅበራዊ ፍትሕ አቀንቃኝ ሂና ጂላኒ እንደሚገልጹት፤ ፖሊሶችና አጠቃላይ በፍትሕ ሥርዓቱ ያሉ ሰዎች ጉዳዩን እንዴት መመልከት እንዳለባቸው ስልጠና ያስፈልጋቸዋል።

የተደፈሩ ሴቶች ወደ ፖሊስ ከመሄድ ይልቅ ራሳቸውን በሚያጠፉበት ፓኪስታን፤ እአአ 2002 ላይ በቡድን አስገድደው የደፈሯትን ወንዶች ለፍርድ ያቀረበችው ሙክታር ማይ ጉዳይ አይረሳም።

የፍርድ ሂደቱ ረዥም ነበር። 2011 ላይ በመድፈር ወንጀል ከተከሰሱት ስድስት ወንዶች አምስቱ ማስረጃ የለም ተብሎ ነጻ ተለቀዋል።

በቀለበት መንገድ ላይ ከልጆቿ ጋር ሳለች የተደፈረችው ሴት ጉዳይ፤ ተጎጂዎችን ከመውቀስ ጋር በተያያዘ በርካቶችን አስቆጥቷል።

ከዓመታት በፊት ቢሆን ኖሮ ተጎጂዎችን መውቀስን በመኮነን ተቃውሞ አይሰማም ነበር። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን ፓኪስታን ውስጥ ጠንካራ የሴቶች መብት ተሟጋቾች ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።

የማኅበረሰቡን የተዛባ አመለካከት ነቅሰው ያወጣሉ። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይም እንቅስቃሴ ያደርጋሉ።