ጎርፍ ፡ ጣና ሐይቅ ሞልቶ በዙሪያው ያሉ ከ12 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ለጉዳት አጋለጠ

የፎገራ ጎርፍ

የፎቶው ባለመብት, DEJENE BEKELE

የምስሉ መግለጫ, የፎገራ ጎርፍ
ታትሟል

ባለፈው ዓመት የክረምት ወራት በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የጣና ሐይቅ ከመጠን በላይ በመሙላቱ በሐይቁ ዙሪያ የሚገኙ የመኖሪያ አካባቢዎችን ጨምሮ ሰፊ ቦታ በውሃ ተጥለቅልቋል።

የጣና ሐይቅ በየዓመቱ የክረምት ወራት ወቅት ዝናብ በሚጥልበት ጊዜ የሚሞላ ቢሆንም የዘንድሮው ግን መጠኑ በጣም ከፍተኛ እንደሆነና ምናልባትም ከ30 ዓመት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እንደሞላና ሰፊ ቦታን ማጥለቅለቁን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ቀሲስ ሙሉዬ ተገኘ ነዋሪነታቸው የጣና ሐይቅን ተጎራብቶ በሚገኘው በፎገራ ወራዳ ናበጋ ቀበሌ ነው። የስድስት ልጆች አባት የሆኑት ቄስ ሙሉዬ፤ የጣና ሐይቅ ውሃ ሞልቶ ካፈናቀላቸው አርሶ አደሮች መካከል አንዱ ናቸው።

እንደ እርሳቸው ገለጻ የሐይቁ ውሃ መስኩን አልፎ ቤታቸውን ስላጥለቀለቀው የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት ለመታደግ መኖሪያቸውን ለቀው ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ ተገደዋል።

በቤት ውስጥ ከነበራቸው ንብረት መካከል ለዕለት ምግብ የሚሆንና እንስሳትን ብቻ ይዘው ራቅ ብለው ወደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው በመሄድ ተጠግተው እየኖሩ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አራት ጥማድ መሬት እንዳላቸው የሚናገሩት ቄስ ሙሉዬ፤ ቢያንስ ሦስት ጥማድ የሩዝ ማሳቸው ከጣና ሐይቅ ተገፍቶ በመጣው የእምቦጭ አረም ተሸፍኖ ከጥቅም ውጪ በመሆኑ በአሁኑ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ሕይወታቸው ላይ ከባድ ችግር እንደተደቀነ አመልክተዋል።

"የውሃ ሙላቱ ያስከተለው ጉዳት ጊዜያዊ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ሕይወታችንን የምንመራበትን አዝመራም አውድሞብናል" ይላሉ።

በተመሳሳይ በጣና ሐይቅ የውሃ ሙላት ከተጥለቀለቁት አካባቢዎች አንዱ በሆነው በፎገራ ወረዳ ዋገጠራ ቀበሌ የሚኖሩት ዲያቆን ድምጸ በዚሁ ሳቢያ ሥራቸውና ሕይወታቸው መስተጓጎል እንደገጠመው ይናገራሉ።

ዲያቆን ድምጸ ኑሯቸውን በንግድ የሚመሩና የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦችን ለአካባቢው ነዋሪ በማቅረብ የችርቻሮ ንግድ እያካሄዱ ጎን ለጎን ደግሞ የእርሻ መሬት ተከራይተው ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለማግኘት የግብርና ሥራን ነበር።

ባለፈው ዓመትም አንድ ሄክታር ተኩል መሬት ከግለሰብ 45 ሺህ ብር ከፍለው ለአንድ ዓመት ተከራይተው ሩዝ ተክለው፣ ከሩዙ መነሳት በኋላ ደግሞ በበልጉ ወቅት ደግሞ ጤፍ ለማምረት አቅደው ነበር።

ነገር ግን ሁሉም ነገር እንደ ዕቅዳቸው ሳይሆን የጣና ሐይቅ ሞልቶ በዙሪያው ያሉ አካባቢዎችን በከፍተኛ መጠን በማጥለቅለቁ ብዙ ብርና ጉልበታቸውን ያፈሰሱበት የእርሻ መሬት በውሃው ተሸፍኗል። በዚህም ሩዝ የተከሉበት ማሳ ከሐይቁ በመጣው የእምቦጭ አረም ተሸፍኖ ማሳው ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ እንደሆነባቸው በሐዘን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህ ጉዳትም ከዲያቆን ድምጸ በተጨማሪ ቢያንስ 180 የሚሆኑ ጎረቤቶቻቸው ላይ እንደደረሰና ብዙዎቹ ከሚኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለው ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ መገደዳቸውን ተናግረዋል።

እሳቸው ግን ለንግድ ያመጧቸውን የሸቀጦችን ይዘው መውጣት ባለመቻላቸው ሁለት ሕጻናት ልጆቻቸውን ይዘው ከውሃ ሙላት ጋር እየኖሩ ነው። በመሆኑም መንግሥት ፈጥኖ እንዲደርስላቸውና ሕይወታቸውን እንዲያተርፍላቸው ተማጽነዋል።

የፎገራ ጎርፍ

የፎቶው ባለመብት, DEJENE BEKELE

የምስሉ መግለጫ, የፎገራ ጎርፍ

የውሃ መጥለቅለቁ የጣና ሐይቅን በሚጎራበቱት በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ ውስጥ ሦስት ቀበሌዎች፣ በፎገራ ወረዳ ሁለት ቀበሌዎችና በደራ ወረዳ አንድ ቀበሌ በድምሩ 6 ቀበሌዎች ውሃ መዋጣቸውን በደቡብ ጎንደር ዞን የአደጋ መከላከል መምሪያ ውስጥ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ስዩም አስማረ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት በሚያጋጥም የውሃ መጥለቅለቅ ሳቢያ እነዚህ ቀበሌዎች እንዳሁኑ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በመጠኑም ቢሆን ችግር ይደርስባቸው እንደነበር የገለጹት ቡድን መሪው የዘንድሮው ግን የተለየና ከፍተኛ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የውሃ መጥለቅለቁ ባጠቃቸው በእነዚህ ስድስት ቀበሌዎች ውስጥ ከ12,500 በላይ ሰዎች በአደጋው ተጠቂ በመሆናቸው ወደ ሌላ ቦታ ለመውሰድ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት አቶ ስዩም፤ እስካሁን ከ2,500 በላይ ነዋሪዎችን ከነበሩበት አካባቢ አውጥቶ ወደ ሌላ ቦታ መውሰድ መቻሉን ተናግረዋል።

"የዘንድሮውን የውሃ ሙላት የከፋ ያደረገው የእምቦጭ አረም ከሐይቁ ውሃ ጋር አብሮ መምጣቱ ነው" ያሉት አቶ ስዩም፤ በዚህም ምክንያት ችግር ከገጠማቸው ሰዎች በተጨማሪ በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ እንስሳትም የሚመገቡት አጥተው ችግር ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል።

ከጣና ሐይቅ አልፎ በመጣው ውሃ የተጥለቀለቁት አካባቢዎች በአብዛኛው የሩዝ ምርት በማምረት የሚታወቁ ሲሆን በእዚህ ወቅትም የአርሶ አደሮቹ ማሳ በሩዝ ምርት ሙሉ በሙሉ የሚሸፈንበት ጊዜ ነበር።

ነገር ግን የሩዝ ማሳው ለሐይቁ ህልውና ትልቅ ስጋት ሆኖ በቆየውና በውሃው ሙላት ተገፍቶ በመጣው የእምቦጭ አረም በመሸፈኑ የአርሶ አደሮቹ ማሳ ከጥቅም ውጪ መሆኑን እንደሆነና በዚህ ምክንያትም እስከ 6 ሺህ ሄክታር የሩዝ ማሳ በእምቦጭ አረም ሊወድም እንደሚችል ቡድን መሪው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የአደጋው ተጠቂዎችን ካሉበት በውሃ የተሸፈነ አካባቢ የማውጣቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ የተናገሩን አቶ ስዩም ጀልባ፣ ጋሪ እና ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም ሰዎችን እና እንስሳትን ወደ ኮረብታማ ቦታ በማዘዋወር አስፈላጊ የምግብ እና የጤና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አቶ ስዩም ገልጸዋል።