ላሚን ዲያክ፡ የቀድሞው የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዚደንት በሙስና ወንጀል የ4 ዓመት እስር ተፈረደባቸው

ታትሟል

የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (አይኤኤኤፍ) የቀድሞ ፕሬዚደንት ላሚን ዲያክ፤ በሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው አራት ዓመት በእስር እንዲያሳልፉ ውሳኔ ተላለፈባቸው።

ሌሎች ሁለት ግለሰቦች ደግሞ ከሥራ መታገዳቸው ተገልጿል።

የ87 ዓመቱ ሴኔጋላዊ ከአበረታች መድሃኒት ጋር ተያይዞ በሙስናና በገንዘብ ዝውውር ነው ክስ የቀረበባቸው።

ዲያክ አበረታች መድሃኒት ይጠቀማሉ ተብለው ከተጠረጠሩ አትሌቶች የምርመራ ውጤታቸውን ለመደበቅ እና የ2012ቱ የለንደን ኦሎምፒክን ጨምሮ ውድድር ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ ጉቦ በመቀበል ጥፋተኛ ተብለዋል።

የቀድሞ ፕሬዚደንቱ የ500 ሺህ ዩሮ ቅጣትም ተጥሎባቸዋል።

ዲያክ የአትሌቶቹን ጉዳይ ለመሸፋፈን ከ3 ሚሊየን ዩሮ በላይ ገንዘብ ተቀብለዋል የሚል ክስ ከቀረበባቸው በኋላ የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ለ አራት ዓመታት ምርመራ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

ውሳኔውን ያስተላለፉት ዳኛም የቀድሞ ፕሬዚደንቱን ድርጊት "የአትሌቲክስን እሴትና አበረታች መድሃኒት ላይ የሚደረገውን ትግል የጣሰ " ብለውታል።

ዲያክ ከህዳር 2015 ጀምሮ በፓሪስ በቁም እስር ላይ ነበሩ።

የቀድሞ ፕሬዚደንቱ በዓለም ስፖርት የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ግለሰቦች አንዱ የነበሩ ሲሆን በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በአሁኑ የዓለም አትሌቲክስ ለ16 ዓመታት አገልግለዋል።

በእንግሊዛዊው ሎርድ ሴባስቲያን ኮ የተተኩትም ከአምስት ዓመታት በፊት ነበር።