ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሬጌን ለዓለም ያስተዋወቀው ሙዚቀኛ በ77 ዓመቱ አረፈ
የሬጌ ፈር ቀዳጅ ከሚባሉት መካከል አንዱ የሆነው ታዋቂው ጃማይካዊ አቀንቃኝ ፍሬደሪክ ናትናኤል ''ቱትስ'' ሂበርት በ77 ዓመቱ ከዚህ ዓመት በሞት ተለየ።
ዝነኛው ሙዚቀኛ በሬጌ እና ስካ የሚታወቀውን ቱትስ ኤንድ ዘ ማይታላስ የሚባለውን የሙዚቃ ቡድን ከአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ ጀምሮ በመምራት ይታወቃል።
ሂበርት ሕይወቱ ያለፈችው በሰላማዊ መንገድ ጃማይካ ኪንግስተን ውስጥ እንደሆነና በወቅቱ በወዳጅ ዘመዶቹ ተከብቦ እንደነበረ የሙዚቃ ባንዱ ትላንት አርብ አስታውቋል።
ምንም እንኳን የሬጌው ፈር ቀዳጅ በምን ምክንያት ሕይወቱ እንዳለፈች ባይታወቅም በኮሮረናቫይረስ ከተያዘ በኋላ ላለፉት ሁለት ሳምንታት የጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ቆይቶ ነበር።
ሂበርት የሬጌ ሙዚቃ አይነትን ለዓለም በማስተዋወቅና እንደውም ሬጌ የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በመጠቀሙ ይታወቃል። በአውሮፓውያኑ 1968 ''ዱ ዘ ሬጌ' በሚለው ዘፈኑ ነው ሬጌን ለዓለም ያስተዋወቀው።
ሂበርት ከሚታወቅባቸው ሌሎች ዘፈኖች መካከል 'ፕሬዠር ድሮፕ'፣ 'ስዊት ኤንድ ዳንዲ፥ እንዲሁም '54-46 ዛትስ ማይ ነምበር' የሚጠቀሱ ናቸው።
የሂበርት ባንድ ባወጣው መግለጫ ላይ ቤተሰቦቹ በሆስፒታል ቆይታው ለተንከባከቡት የጤየ ባለሙያዎች ምስጋናቸውን እንዳቀረቡ ገልጿል።
ሂበርት ባለትዳርና የስምንት ልጆች አባት ነው።
የሂበርት ሞት የተሰማው የሙዚቃ ባንዱ ከአስር ዓመታት በላይ ቆይታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ 'ጎ ቱ ቢ ታፍ' የተሰኛውን አልበሙን ከለቀቀ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ነው።
ሮሊንግ ስቶን ባሳለፍነው ወር እትሙ ሂበርትን ''የዓለም እጅግ ምርጡ የሬጌ ሙዚቀኛ'' በማለት አሞካሽቶት ነበር። አክሎም የዓለማችን ምርጥ 100 ሙዚቀኞች ዝርዝር ውስጥ አስገብቶታል።
የሂበርትን ሞት ተከትሎ በርካቶች ሀዘናቸውን በማህበራዊ ሚዲያ በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
የዩኬው ታዋቂ ተዋናይና ቀልደኛ ሰር ሌኒ ሄንሪ የእሱን ሞት በመስማቴ ''በጣም አዝኛለሁ'' ብሏል። ''በቤታችን ስናድግ የእርሱ ሙዚቃ ሁኔም ይከፈት ነበር'' በማለት በትዊተር ገጹ ላይ ጽፏል።
ሌላኛው የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኝና የቦብ ማርሌ ልጅ ዚጊ ማርሌ በትዊተር ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት ደግሞ ''ለእኔ ልክ እንደ አባት ነበር'' በማለት ገልጾታል።