ማሊ ፡ የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም አገራዊ ውይይት ጀመረች

ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ (ከመሃል) ዋነኛ የአገሪቱን ፖለቲከኞች ሲያነጋግሩ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ (ከመሃል) ዋነኛ የአገሪቱን ፖለቲከኞች ሲያነጋግሩ ነበር
ታትሟል

በማሊ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም የሚካሄደው የሦስት ቀናት አገራዊ ውይይት ዛሬ ሐሙስ በዋና ከተማዋ ባማኮ ተጀምሯል።

ውይይቱ የሚካሄደው በምዕራብ አፍሪካ አገራት መሪዎች በተቀመጠው ቀነ ገደብ ሲሆን መሪዎቹ እስከ አውሮፓውያኑ መስከረም 15 ድረስ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋሙ የጊዜ ገደብ አስቀምጠዋል።

የአገሪቱን መንግሥት የተቆጣጠሩት የማሊ ወታደራዊ መሪዎች ላይ የሲቪል መንግሥት እንዲያቋቁሙ ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸው ነው።

ከፍተኛ የወታደራዊ መሪዎቹም በሕዝቡ ዘንድ ያላቸውን ምስል ለማስተካከልና በዓለም አቀፉ ማልበረሰብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነትን ለማጠናከር በማሰብ በርካታ ቁልፍ የሚባሉ የአገሪቱ ፖለቲከኞችና ምሁራንን እያነጋገሩ ነው።

መፈንቅለ መንግሥቱን ካቀነባበሩት መካከል አንድ የወታደራዊ ማሰልጠኛ አካዳሚ ምክትል ኃላፊና በፈረንሳይ ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱ ጄኔራሎች አሉበት።

ኮሎኔል ጎታ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዲዮንኮንዳ ትራዎሬ እና አዳሙ ቱማኒ ቱሬንም ጭምር ያነጋገሩ ሲሆን ሁለቱም መሪዎች ሰላማዊ የመንግሥት ሽግግር ለማድረግ የቻሉና በማሊ እስላማዊ ከፍተኛ ካውንስል ውስጥ ተቀባይነት ያላቸው ናቸው።

ትላንትና ደግሞ ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን ሁለት የጥናት ወረቀቶችን ያቀረበ ሲሆን እነዚህ ሰነዶች ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት ለሚካሄደው አገራዊ ውይይት መሰረት እንደሚሆኑ ተገልጿል።

ማሊ አባል የሆነችበትና አስራ አምስት አባላት ያሉት የምዕራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) ልዑካን ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ ማሊን መጎብኘታቸው የሚታወስ ነው።

በቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ጉድ ላክ ጆናታን የሚመራው የልዑካን ቡድን ስልጣኑን ከተቆጣጠረው ወታደራዊ ኃይልና ከስልጣን ከተወገዱት ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ባውባካር ኬታ ጋር ተወያይተዋል።

ከስልጣን የተወገዱት የማሊ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ባውባካር ኬታ ደግሞ ታመው ለህክምና ወደ አቡዳቢ መሄዳቸው የተሰማው ባሳለፍነው ሳምንት ነበር።

የ75 ዓመቱ ፕሬዚዳንት በደም ዝውውር መታወክ (ስትሮክ) ታመው ወደተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መዲና አቡዳቢ ማቅናታቸውን የአገሪቱ ወታደራዊ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ሙስና፣ የምጣኔ ሀብት ኢ-ፍትሃዊ ክፍፍልና አወዛጋቢ የምርጫ ሕግን በተመለከተ ተቃውሞን ከማሰማት ባለፈ፤ የሁሉም መሰረታዊ ጥያቄ ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን እንዲወርዱ ነበር። ይህንንም ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ በመፈንቅለ መንግሥት ወርደዋል።

የማሊ መፈንቅለ መንግሥት በርካታ ማሊያውያንን አስደስቷል፤ ጮቤ የረገጡ ማሊያውያንም በየጎዳናው በመውጣት ደስታቸውንም ገልጸው ነበር።

ነገር ግን በመፈንቅለ መንግሥቱ ደስተኛ ያልሆኑት በርካቶች ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የበርካታ አገራት መሪዎች ድርጊቱን ሲያወግዙት የአፍሪካ ሕብረት ደግሞ ማሊን ከአባልነት አግዷታል።

ሰፊ የቆዳ ሽፋን ያላት ማሊ ግዛቷ የሰሃራ በረሃንም የተወሰነውን የሚሸፍን ሲሆን፤ የፈረንሳይ ወታደሮችን ጨምሮ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪዎች አክራሪ ፅንፈኝነትን እንዋጋለን በሚልም ሠራዊት አስፍረውባታል።

የማሊን ፕሬዚዳንት በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከስልጣን ያስወገዱት ወታደራዊው ቡድን ሽግግሩን የሚያሳልጥ አንድ የሲቪል መሪ እንዲሰይሙ የአንድ ሳምንት ጊዜ የተሰጣቸው ደግሞ ባሳለፍነው ሳምንት ነበር።

ማሊ አባል የሆነችበትና አስራ አምስት አባላት ያሉት የምዕራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መሪዎች እንዳሉት ቡድኑ የሚያቀርባቸው ሲቪሎች ጠቅላይ ሚኒስትርና ፕሬዚዳንት በመሆን አገሪቷን ይመራሉ።

ለሦስት ቀናት የሚካሄደው አገራዊ ውይይትም ለእነዚህና ሌሎችም ማሊን ሊገጥሟት ሰለሚችሉ ጥያቄዎች መልስን ይዞ እንደሚጠናቀቅ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል።