ናይጄሪያ፡ ቡሃሪ የምዕራብ አፍሪካ አገራት መሪዎችን ሕገ መንግሥታችሁን አክብሩ አሉ

የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ሙሃመዱ ቡሃሪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ሙሃመዱ ቡሃሪ የምዕራብ አፍሪካ አገራት በሕገ መንግሥታቸው ላይ የተቀመጠውን የስልጣን ዘመን እንዲያከብሩ ጥሪ አቀረቡ።

ፕሬዝዳንቱ አስተያየታቸውን የሰጡት የአይቮሪ ኮስት እና የጊኒ አቻዎቻቸው ለሶስተኛ ጊዜ ሊወዳደሩ መወሰናቸውን ተከትሎ ነው።

የፕሬዝዳንት ቡሃሪ አስተያየት የተሰማው በኒጀር በተካሄደው የምዕራብ አፍሪካ አገራት ምጣኔ ሃብት ማህበረሰብ፣ ኢኮዋስ ፣ ስብሰባ ላይ ነው።

የአይቮሪ ኮስቱ ፕሬዝዳንት አላሳኔ ኦኣታራ ለሶስተኛ ጊዜ ለመወዳደር የወሰኑት በድንገት ይተኳቸዋል ተብሎ ሲታሰቡ የነበሩት ግለሰብ መሞትን ተከትሎ ነው። የፕሬዝዳንቱ ተቀናቃኞች ውሳኔው ኢ ሕገመንግሥታዊ ነው በማለት ተቃውመውታል።

የ82 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ኮንዴ በሚያስተዳድሯት ጊኒም አመጽ የተቀላቀለበት የተቃውሞ ሰልፍ እየተካሄደ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱ በመጪው ጥቅምት በሚካሄደው ምርጫ ለሶስተኛ ጊዜ አእንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።

ሰኞ ዕለት ለአንድ ቀን በተካሄደው የኢኮዋስ ስብሰባ ስምንት የአገራት መሪዎች፣ የጋና ሴኔጋልና ቡርኪናፋሶ ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ ተገኝተው ተሳትፈዋል።

በስብሰባው ላይ በማሊ ያለው አለመረጋጋት ተነስቶ ውይይት መደረጉ ተገልጿል።

በነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ በማሊ መፈንቅለ መንግሥት ተደርጎ ወታደራዊ አስተዳደር መመስረቱን በመቃወም፣ ወደ ሲቪል አስተዳደር በፍጥነት አገሪቱ አንድትመለስ ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ ቀደም፣ ኢኮዋስ በማሊ ላይ ማዕቀብ ጥሎ በዓመት ውስጥ ምርጫ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የማሊውን ፕሬዝዳንትን አስወግዶ ስልጣን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ኃይል ስልጣኑን አገሪቱን ወደ ሽግግር ለሚመራ የሲቪል አስተዳደር በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዲያስረክብ የምዕራብ አፍሪካ አገራት መሪዎች ቀነ ገደብ አስቀምጠዋል።

ለወታደራዊ ኃይሉ አንድ ሳምንት እድሜ ብቻ የተሰጠው ሲሆን የሚመሰረተው የሲቪል ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር አገሪቱን ወደ አዲስ ምርጫ የምታደርገውን ጉዞ ይመሩታል ብለዋል።

ሰኞ እለት የኢኮዋስ አባል አገራት ፕሬዝዳንቶች በኒጀር ዋና ከተማ ኒኣሜ ተሰብስበው ባሳለፉት ውሳኔ ላይ ወታደራዊ ኃይሉ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።

ኢኮዋስ ሽግግሩ በዓመት ውስጥ መካሄድ አለበት ብሎ የጊዜ ገደብ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት ወታደራዊ ኃይሉ ግን " በቂ የሆነ ጊዜ" እንዲሰጠው በመግለጽ ቢያንስ ሁለት አመት እንደሚያስፈልገው አስታውቆ ነበር።

ወታደሩ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ስለ ሽግግሩ ሂደት በመነጋገር ላይ ይገኛል ተብሏል።

ከስልጣን በጦር ኃይሉ የተወገዱት ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ቦውባካር ኬታ ቅዳሜ ዕለት ወደ ተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ለሕክምና ማቅናታቸውም ተሰምቷል።

ወታደሩ ፕሬዝዳንት ኬታ ሕክምናቸውን ጨርሰው በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ውስጥ ወደ ማሊ መመለስ አለባቸው ሲል አስታውቋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ስብሰባቸውን ሲያደርጉ የነበረው በኢንተርኔት ሲሆን አሁን ግን በአካል ተገናኝተው በቀጠናቸው ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል።