መካከለኛው ምሥራቅ ፡ ከእስራኤል ወደ አረብ ኤምሬትስ የመጀመሪያው የንግድ በረራ ሊደረግ ነው

የእስራኤል አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

ከእስራኤል ወደ አረብ ኤምሬትስ ለመጀመሪያ ጊዜ የንግድ በረራ ሊካሄድ ነው። ይህም በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት ጤናማ እየሆነ ስለመምጣቱ ጠቋሚ ነው ተብሏል።

የእስራኤሉ ኤል አል አየር መንገድ የእስራኤል ልዑካንን እንዲሁም የአሜሪካ ባለሥልጣኖችን ይዞ የሦሰት ሰዓት በረራ ያካሂዳል።

አውሮፕላኑ በሳዑዲ አየር ክልል እንዲበር ይፈቀድለታል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ቀደም የእስራኤል አውሮፕላን በአየር ክልሉ ማለፍ አይችልም ነበር።

በመካከለኛው ምሥራቅ፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እስራኤል ከተመሠረተች ወዲህ እውቅና የሰጠ ሦስተኛው የአረብ አገር ናት።

አረብ ኤምሬትስ እስራኤል ላይ ከ1972 አንስቶ ተጥሎ የነበረውን ገደብ ቅዳሜ አንስታለች። በወሩ መባቻ ላይ ቀጥታ የስልክ መስመር ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ መጀመሩ ይታወሳል።

በእስራኤል እና በአረብ ኤምሬትስ መካከል ያለው ግንኙነት የተለሳለሰው በአሜሪካ አሸማግይነት ሲሆን፤ ነሐሴ 13 ነበር ወዳጅነታቸውን ይፋ ያደረጉት።

በአብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ይህ ዜና በመልካም ቢወሰድም፤ ፍልስጤም ግን ተቃውሞዋን ገልጻለች። በተለይም የአረብ ኤምሬትስ ለፍልስጤም እውቅና ካልሰጠችው እስራኤል ጋር ግንኙነት መፍጠራቸው፤ ፍልስጤምን መክዳት ነው ተብሏል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ከአረብ ኤምሬትስ ጋር ዳግመኛ መወዳጀታቸውን አስታከው በወረራ የተያዘውን ዌስት ባንክ በግዳጅ የእስራኤል ይዞታ የማድረግ እቅዳቸውን ለማዘግየት ተስማምተዋል።

ፍልስጤም ይዞታው አገር የምመሠርትበት ነው ትላለች።