በኡጋንዳ አስር ልጆች በመብረቅ ተመተው ሞቱ

ታትሟል

በሰሜን ምዕራብ ኡጋንዳዋ አሩዋ ከተማ አስር ልጆች በመብረቅ ሳቢያ ሕይወታቸው አለፈ።

ልጆቹ ከዝናብ ለመሸሽ ጎጆ ቤት ውስጥ ተጠልለው ነበር።

ታዳጊዎቹ እግር ኳስ እየተጫወቱ ሳለ ከፍተኛ ዝናብ ሲጥል ጨዋታውን አቋርጠዋል። ከዛም በሳር የተሠራ ጎጆ ውስጥ ተጠልለው ሳለ ጎጆው በመብረቅ ተመትቷል።

ከልጆቹ መካከል ዘጠኙ ከ13 ዓመት እስከ 15 ባለው እድሜ ክልል ውስጥ ናቸው። ሕይወታቸው ያለፈው በመብረቅ የተመቱበት ቦታ ሲሆን፤ ከታዳጊዎቹ አንዱ ሆስፒታል ከገባ በኋላ መሞቱ ታውቋል።

ከአደጋው የተረፉ ሦስት ልጆች ደግሞ ሕክምና እየተደረገላቸው ይገኛል።

የኡጋንዳ ሰሜን ምዕራባዊ አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ ይዘንባል። በአካባቢው በተደጋጋሚ መብረቅም ይከሰታል።

ከጎርጎሮሳውያኑ 2011 ወዲህ ኡጋንዳ ውስጥ እንዲህ ያለ የከፋ አደጋ ሲደርስ ይህ የመጀመሪያው ነው።

2011 ላይ በማዕከላዊ ምዕራብ ኡጋንዳ 18 ታዳጊዎች ትምህርት ቤት ሳሉ ሞተዋል።

በዛው ዓመት በአንድ ሳምንት ውስጥ 28 ሰዎች በመብረቅ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።