አር. ኬሊ እሥር ቤት ውስጥ ተደብድቧል - ጠበቃው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካዊው ድምጻዊ አር. ኬሊ ጠበቃ ደንበኛቸው በሌላ እሥረኛ 'በመደብደቡ ምክንያት' ከእሥር ወዲያውኑ እንዲለቀቅ ጠየቁ።
ስቲቭ ግሪንበርግ የተባሉት ጠበቃ እንዳሉት አር ኬሊ በቺካጎ ሜትሮፖሊታን ማረሚያ ቤት እያለ በሌላ እሥረኛ ድብደባ ተፈፅሞበታል።
አንድ ሰሞን ብዙዎች ያበዱለት ሙዚቀኛ የነበረው አር. ኬሊ ወሲባዊ ጥቃት በማድረስ ተጠርጥሮ ፍርዱን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
ጠበቃው በትዊተር ገፃቸው ላይ እንዳስታወቁት የደንበኛቸው ኬሊ የጉዳት መጠን እስካሁን አልታወቀም።
ኬሊ በተለይ ታዳጊዎች ላይ ወሲባዊ ጥቃት በማድረስና በወሲብ ንግድ በመሰማራት ነው የተከሰሰው።
ቲኤምዚ የተሰኘው የታዋቂ ሰዎችን ገመና በማጋለጥ የሚታወቀው ጣቢያ እንደዘገበው አር. ኬሊ እሥር ቤት ውስጥ አልጋው ላይ ቁጭ ብሎ ሳለ ነው በሌላ እሥረኛ የተደበደበው።
ደብዳቢው፤ ኬሊ ይፈታ ብለው ከእሥር ቤቱ ውጭ ተቃውሞ በሚያሰሙ ሰዎች ምክንያት የማረሚያ ቤቱ አስተዳዳሪዎች ቤተሰብ መጥቶ መጠየቅ አይችልም ማለታቸውን ተከትሎ በንዴት ነው ሙዚቀኛው ላይ ጉዳት ያደረሰው ተብሏል።
ጠበቃው፤ "ሁሌም አር. ኬሊ ይፈታ ብለው የሚጠይቁ ሰዎች ሲመጡ እሥር ቤቱ ሙሉ በሙሉ ይዘጋል" ብለዋል።
አር. ኬሊ፤ ሦስት ጊዜ ይግባኝ ጠይቆ ከእሥር እንዲፈታ ቢማፀንም አልተፈቀደለትም። ብሩክሊን ውስጥ ይግባኝ የከለከሉት ዳኛ ምስክሮችን ሊያስፈራራ ይችላል ሲሉ ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል።
የሙዚቀኛው የፍርድ ሂደት በሚቀጥለው ወር ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል። የሙዚቀኛው ጠበቃዎች ግን ደንበኛቸው በደኅንነት ስጋት ምክንያት ከእሥር እንዲለቀቅ ጠይቀዋል።
የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ቃል አቀባይ ሙዚቀኛው ተደብድቧል ወይ ተብለው ተጠይቀው አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ጠበቃው ደንበኛው ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰበት ለማጣራት ያደረጉት ሙከራ እንዳልተሳካላቸው አሳውቀዋል።
"ጉዳቱ ቀላል እንዲሆን ነው ምኞታችን" ሲሉም ፅፈዋል።
በ1990ዎቹ የአርኤንድቢ ሙዚቃ ዘውግ ንጉሥ የነበረው ኬሊ ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜ እሥር ቤት አሳልፏል። በሦስት የተለያዩ ግዛቶች ክስ የተመሰረተበት ሙዚቀኛው ፍርዱን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።













