ማዳጋስካር፡ እስር ቤት ውስጥ በተነሳ ግጭት 20 እስረኞች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በማዳጋስካር ባለሥልጣናት በአገሪቷ ደቡባዊ ክፍል በሚገኝ እስር ቤት የተነሳን ግጭት ለማስቆም ባደረጉት ሙከራ 20 እስረኞች መገደላቸውን የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በፋራፋጋና እስር ቤት የተነሳው ግጭት የጀመረው ትናንት አመሻሽ 12 ሰዓት ላይ ሲሆን እስረኞቹ ለሁለት ቡድን ተከፍለው ጠባቂዎቻቸውን በድንጋይ ሲያጠቁ እንደነበር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በፌስቡክ ገፁ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
እስረኞቹ መሳሪያ መጠቀማቸውንም መግለጫው አክሏል።
ባለሥልጣናት ግጭቱን ለመቆጣጠር ባደረጉት ጥረት ከተገደሉ 20 እስረኞች በተጨማሪ ስምንት ታሳሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ሚኒስቴሩ ሌሎች 29 እስረኞች እንደገና መያዛቸውን ገልፆ፤ ነገር ግን 31 እስረኞች እስካሁን እንደጠፉ መሆናቸውን ጠቅሷል።
ጥቃቱ እንዴትና በምን ምክንያት እንደጀመረ ግልፅ ባይሆንም ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ የማዳጋስካር እስር ቤቶች የፈራረሱ፣ አስፈላጊ ነገሮች ያልተሟሉበት፣ የገንዘብ ፣ የቁሳቁስ እና አጠቃላይ የድጋፍ እጥረት ያለባቸው መሆኑን ከሁለት ዓመታት በፊት ባወጣው ሪፖርቱ አስታውቋል።
ሪፖርቱ እስረኞቹ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለዓመታት በእስር እንደሚቆዩም ጠቅሷል።
ባለፈው ዓመትም የቢቢሲው ፑምዛ ፊሃልኒ በአገሪቷ በአንታላሃ እስር ቤት ውስጥ ስላለው ሁኔታ ዘገባ ሰርቶ ነበር።














