ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ደቡብ ሱዳን፡ ዕቃ ጫኝ አውሮፕላን ተከስክሶ ስምንት ሰዎች ሞቱ
በደቡብ ሱዳን ለተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሰራተኞች ደመወዝ ለማድረስ በጉዞ ላይ የነበረ እቃ ጫኝ አውሮፕላን በዋና መዲናዋ ጁባ አቅራቢያ ተከስክሶ ተሳፍረው ከነበሩ 9 ሰዎች ስምንቱ መሞታቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ከአደጋው የተረፈው ግለሰብ በሆስፒታል ሕክምና እየተደረገለት እንደሚገኝ ተገልጿል። አደጋው የተከሰተው ከጁባ አውሮፕላን ማረፊያ ከተነሳ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ነበር ተብሏል።
'አንቶኖቭ 36' አውሮፕላን በምዕራባዊዋ ባሀር ኢል ጋዛል ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ዋዩ ለሚገኙ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሰራተኞች ደመወዝ ለማድረስ በኦፖርቹኒቲ ባንክ ነበር የተላከው።
የአገሪቷ ትራንስፖርት ሚኒስትር ባዱት ቢያር የል፤ የገንዘብ መጠኑም 35 ሺህ ዶላር እንደነበር እንደተነገራቸው ገልፀው፤ "ይህም በአደጋው ወደ አመድነት ተቀይሯል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአደጋውን ምክንያት ለማጣራትም ኮሚቴ መዋቀሩን ሚኒስትሩ አክለዋል።
ቅዳሜ እለት በተከሰተው በዚህ አደጋ ሕይወታቸው ካለፈው መካከል አራቱ ደቡብ ሱዳናዊ ሲሆኑ ሁለቱ ታጂኪስታን ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ ዩክሬናዊ መሆናቸው ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ባስተላለፉት የሃዘን መልዕክት ጠቅሰዋል።
ፕሬዚደንቱ በመልዕክታቸው " በዚህ አሳዛኝ አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች ሁላችንም ጥልቅ ሃዘን ተሰምቶናል፤ እኩልም ተጨንቀናል" ብለዋል።