መካከለኛው ምሥራቅ፡ ፍልስጤም የኮነነችውን ስምምነት የትራምፕ ዋና አማካሪ አሞካሹ

የፎቶው ባለመብት, EPA
እስራኤልና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከስምምነት መድረሳቸውን ተከትሎ ከተለያዩ ወገኖች በስምምነቱ ላይ ድጋፍና ተቃውሞ እተሰማ ነው።
ከእነዚህም ውስጥ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋና አማካሪ ጃሬድ ኩሽነር፤ በአሜሪካ አማካይነት እስራኤልና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የደረሱበት የሰላም ስምምነት በመካከለኛው ምሥራቅ “ትልቅ ለውጥ” ያሳያል አሉ።
ከሲቢኤስ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ስምምነቱ ቀጠናውን ሰላማዊ ያደርጋል ብለዋል።
ይህ ስምምነት በመካከለኛው ምሥራቅ የአረብ-እስራኤል ሦስተኛው ስምምነት ሲሆን፤ በዚህም የባህረ ሰላጤው አገር ሲካተት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስምምነቱን ቢያሞግስም፤ ፍልስጤም፣ ኢራንና ቱርክ ኮንነውታል።
እስራኤልና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሦስት ሳምንት ውስጥ ስምምነቱን ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል። ስምምነቱ በአገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ጤናማ የሚያደርግ ነው የተባለ ሲሆን፤ አንዳቸው በሌላው ግዛት ኤምባሲ እንደሚከፍቱም ይጠበቃል።
እስራኤል አገር ከተመሰረተችበት እአአ በ1948 ወዲህ የአረብ ኤምሬቶችን ጨምሮ ከሌሎች ከመካከለኛው ምሥራቅ እንዲሁም ከሰሜን አፍሪካ አገራት ጋር ለዘመናት በዘለቀ ፍትጫ ውስጥ ቆይታለች። ይህም ሁኔታ ከግብፅና ከዮርዳኖስ ጋር የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ እየረገበ መጥቷል።
እስራኤልና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የቀጠናው ስጋት ብለው የሚያስቡት ኢራንን ነው።
ትራምፕ ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ አማካሪያቸው ጃሬድ ኩሽነር እስራኤልና አረብ ኤምሬቶችን ለማሸማገል ሲሞክሩ ነበር።
“ስምምነቱ ትልቅ እርምጃ ነው። መካከለኛው ምሥራቅን ሰላማዊ ስለሚያደርግ በቦታው መኖር ያለባቸውን የአሜሪካ ወታደሮች ቁጥር ይቀንሳል። ስምምነቱ ለትራምፕ ድል ነው። ለቀጠናውም ተስፋ ይሰጣል” ብለዋል።
ስምምቱ ይፋ ከመደረጉ ከስምንት ወራት በፊት ትራምፕ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል ሰላም ያወርዳል ያሉትን ሐሳብ ማስታወቃቸው ይታወሳል። ያኔም አሸማጋዩ አማካሪያቸው ኩሽነር ነበሩ።
እስራኤል ሐሳቡን ብትደግፍም፤ ፍልስጤም በበኩሏ ለእስራኤል የወገነ ነው ብላ ዕቅዱን ውድቅ አድርጋዋለች። ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ያላትን ግንኙነትም ገታለች።
ስምምነቱ ለፍልስጤም ምን ማለት ነው?
በስምምነቱ መሠረት፤ በእስራኤልና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይጀመራል።
ስምምነቱ እስራኤል በወረራ የተያዘውን ዌስት ባንክ ወደ ግዛቷ ለማካተት ያላትን እቅድ በጊዜያዊነት ያስቆማል። ይህም ጉዳይ በእስራኤልና በፍልስልጤም መካከል አለመግባባት ከፈጠሩ ነገሮች ግንባር ቀደሙ ነው።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ በዌስት ባንክ 30 በመቶ ግዛት በመያዝ “የእስራኤልን ሉአላዊነት” ለማስጠበቅ ቃል ገብተዋል።
ፍልስጤም ይህ ቦታ ይዞታዋ እንደሆነ ትገልጻለች። ቦታውን ማጣት ፍልስጤምን እንደ ነፃ አገር ለማቆም በሚደረገው ጥረት ላይ እንቅፋት እንደሚፈጥርም አክላለች።
በቀጠናው ስለ ስምምነቱ ምን ተባለ?
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ከአረብ ኤምሬቶች ጋር የሰላም ስምምነት መፈራረም “እድለኛ መሆን ነው” ካሉ በኋላ “በቀጣይ ጥሩ ግንኙነት እንደሚኖረን ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጪ ጉዳይ ሚንስተር ዶ/ር አንዋር ጋርጋሽ፤ ስምምነቱ “እስራኤል ዌስት ባንክን የግዛቷ አካል ለማድረግ የወጠነችውን እቅድ የሚገታ ነው” ብለዋል።
ባህሬንና ኦማን ስምምነቱን ደግፈዋል። የአሜሪካ የቅርብ ወዳጅ ሳዑዲ እስካሁን በይፋ ያለችው ነገር የለም።
አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን እስራኤልና ፍልስጤም እርቀ ሰላም እንዲያወርዱ የሚደግፍ ንግግር አድርገዋል።
ፍልስጤማውያን ግን በስምምነቱ ተቆጥተዋል። “ክህደት ነው” በማለትም ስምምነቱን ኮንነውታል።
የፍልስጤሙ ፕሬዘዳንት ማሕሙድ አባስ ቃል አቀባይ ነቢል አቡ ሩዲንያ፤ አረብ ኤምሬቶች “ከዚህ አሳፋሪ ስምምነት መውጣት አለባቸው” ሲሉ ተናግረዋል።
ከእራኤል ጋር ቅራኔ ውስጥ ያለችው የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር “ስምምነቱ ፍልስጤምን መክዳት ነው” ሲል አቋሙን ገልጿል።
የፍልስጤም ደጋፊ የሆነችው ቱርክ በበኩሏ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን “ታሪክ ይቅር አይላትም” ብላ፤ ከአረብ ኤምሬቶች ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ልታቋርጥ እንደምትችል አስታውቃለች።














