ኮሮናቫይረስ ፡ ከእንቅስቃሴ ገደቡ በኋላ በደቡብ አፍሪካ ወንጀል በእጅጉ ቀንሷል ተባለ

ታትሟል

በደቡብ አፍሪካ የኮሮረናቫይረስን ተከትሎ በተጣለው እንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ በአገሪቱ ይፈጸም የነበረው የወንጀል መጠን 40 በመቶ መቀነሱን መንግሥት ያወጣው መረጃ አመለከተ።

የፖሊስ ሚኒስትሩ ከባለፈው ሚያዝያ እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ውስጥ ጾታዊ ጥቃትና በጦር መሳሪያ የታገዘ ዝርፊያን ጨምሮ ሌሎች ወንጀሎች በእጅጉ ቀንሰዋል ብለዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም አወዛጋቢነቱ ቢቀጥልም ከወረርሽኙ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በአልኮል ሽያጭ ላይ የተደረገው ክልከላ ለወንጀሎች መቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ካሉ በኋላ፤ በአልኮል መሸጫዎች ላይ የሚፈጸም ዝርፊያና ጥቃት ግን ጨምሯል ብለዋል።

ደቡብ አፍሪካ በዓለማችን ከፍተኛ ወንጀል ከሚፈጸምባቸው አገራት ተርታ ትመደባለች። በተጨማሪም በአፍሪካ በኮሮረናቫይረስ ከተያዙ ሰዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሚገኙት በደቡብ አፍሪካ ነው።

በአገሪቱ ከ500 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 11 ሺህ ሰዎች ደግሞ በዚሁ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። ነገር ግን ቁጥሩ እንዲህ ከፍ ሊል የቻለው በተገቢው መንገድ በርካቶችን መመርመር በመቻሏ እንደሆነ ተገልጿል።

የፖሊስ ሚኒስትሩ ቤኪ ሴሌ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሲሰጡ ''ደቡብ አፍሪካ ከዚህ በፊት አይታው የማታውቀው የወንጀል መቀነስ እያስመዘገበች ነው። ይሄ ለሁላችንም በጣም አስዳሳች ነገር ነው'' ብለዋል።

''ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ካለፈው ዓመት አንጻር ትልልቅ የሚባሉ ወንጀሎች ቀላል የማይባል መቀነስ አሳይተዋል። ባለፉት ሦስት ወራት ደግሞ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል 40.4 በመቶ መቀነሱን አስተውለናል።''

የመንገድ ላይ ዝርፊያ፣ በንግድና መኖሪያ ቤቶች ላይ በጦር መሳሪያ በመታገዝ ይፈጸሙ የነበሩ ወንጀሎች ደግሞ ባለፉት ሦስት ወራት በ29 በመቶ መቀነሳቸውን ሚኒስትሩ አክለዋል።

ደቡብ አፍሪካ ካለፈው መጋቢት ወር አጋማሽ አካባቢ ጀምሮ ማንኛውም አይነት አልኮል እንዳይሸጥ የሚከለክል ሕግ አውጥታ ነበር። ሕጉም እስከ ሰኔ ወር ድረስ የሚቆይ የነበረ ሲሆን ሐምሌ ላይ ግን በድጋሚ ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል።

ሕጉ በወጣ ማግስት የፖሊስ ሚኒስትሩ በቴሌቪዥን ቀርበው ''ሕጉን በመተላለፍ አልኮል የሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ ፈጣንና ተመጣጣኝ እርምጃ እንወስዳለን'' ብለው ነበር።

በርካቶችም አልኮል ሲጠጡ የተገኙ ሰዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ትንሽ ከበድ ያለ ይመስላል በማለት ሚኒስትሩን ሲተቿቸው ነበር። የምግብና መጠጥ ሻጮችም ቢሆኑ ክልከከላው የገቢ ምንጫቸውን የሚጎዳና ሕይታቸውን ከባድ እንደሚያደርግባቸው በተደጋጋሚ ገልጸዋል።