የአውሮፓ እግር ኳስ፡ 26 ጨዋታዎች በሁለት ሳምንት ተኩል ይደረጋሉ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን ጨምሮ፣ የጣልያን፣ ስፔንና ጀርመን ሊጎች ተጠናቀዋል። አሁን ጊዜው የአውሮፓ ሊጎች ነው።
በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለአምስት ወራት ያክል ተቋርጠው የነበሩት የቻምፒየንስ ሊግና የዩሮፓ ሊግ ጨዋታ ዛሬ [ረቡዕ] ምሽት በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀምራሉ።
ማንቸስተር ሲቲና ቼልሲ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ሲፋለሙ፤ ማንቸስተር ዩናይትድና ዎልቭስ በዩሮፓ ሊግ ተሳታፊ ናቸው።
በሚቀጥለው ሁለት ሳምንት ተኩል 26 ጨዋታዎች ይከናወናሉ።
አምስት ጊዜ ቻምፒየንስ ሊግ ያነሳው የጁቬንቱሱ ክርስቲያኖ ሮናልዶና አራት ጊዜ የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ የሳመው የባርሳሌናው ሊዮኔል ሜሲን የምንመለከታቸው ይሆናል።
የዩሮፓ ሊግ ፍፃሜ ነሐሴ 15 ኮሎኝ ውስጥ እንዲካሄድ እቅድ የተያዘለት ሲሆን፤ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ ነሐሴ 17/2012 በፖርቹጋል፤ ሊዝበን ይካሄዳል።
ቻምፒየንስ ሊግ ከመቋረጡ በፊት የመጨረሻውን ጨዋታ ያደረጉት ሊቨርፑልና አትሌቲኮ ማድሪድ ናቸው። በሌላ ስታድየም ደግሞ ፒኤስጂ ከዶርትመንድ ተፋልመዋል። በውጤቱም ሊቨርፑልና ዶርትመንድ ከውድድሩ መሰናበታቸው አይዘነጋም።
አትሌቲኮና ፒኤስጂ አትላንታና የጀርመኑ አርቢ ሊፕዝግን ተከትለው ወደ መጨረሻዎቹ ስምንት አልፈዋል።
ሲቲዎች በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ማድሪድን በቤርናቢዩ ስታድየም 2-1 ረተዋል። ሁለተኛው ዙር ጨዋታ በሲቲ ስታድየም የሚካሄድ ይሆናል።
አሮጊቶቹ በተሰኘ ቅፅል ስማቸው የሚታወቁት ጁቬንቱሶች በሊዮን ሜዳ 1-0 ተረተዋል። የሮናልዶ ቡድን ሁለተኛውን ዙር ጨዋታ ለማሸነፍ ዝተዋል።
ቼልሲ በባየርን ሙኒክ 3-0 እየተመራ ነው ሁለተኛውን ዙር ጨዋታ በሜዳው ስታንፎርድ ብሪጅ የሚያከናውነው። ሌላኛው ጨዋታ በበርሴሎናና በናፖሊ መካከል የሚካሄደው ነው። የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ በናፖሊ ሜዳ 1-1 ነበር የተጠናቀቀው።
የዩሮፓ ሊግ ጨዋታዎች ደግሞ ዛሬ ምሽት ይጀምራሉ።
የመጀመሪያውን ዙር ጨዋታ 5-0 ያሸነፈው ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው የኦስትሪያው ኤልኤኤስኬን ይገጥማል።
ሬንጀርስ ከባየር ሊቨርኩሰን ዎልቭስ ከኦሎምፒያኮስ ሌሎች የዩሮፓ ሊግ ጨዋታዎች ናቸው።
ሁሉም የቻምፒየንስ ሊግ እና የዩሮፓ ሊግ ጨዋታዎች በዝግ ስታድየም የሚደረጉ ናቸው።














