በስፔን ወረርሽኙ ሊያገረሽ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል

Man in Barcelona

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

ቀደም ካለው ሰፋ ያለ የኮሮናቫይረስ መልሶ "ሊያገረሽ ይችላል" ብላ ስጋት ውስጥ ያለችው ስፔን አዳዲስ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው።

በአገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ ውጪ በሚገኙ ከተሞች ውስጥ የበሽታው መስፋፋት እየታየ ሲሆን የካታሎኒያ ግዛት ደግሞ ለሁለት ሳምንታት የምሽት መዝናኛ ቦታዎችን እንዲዘጉ አድርጋለች።

ስፔን ጥላው የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካበቃ ከወር በኋላ ዋና ከተማዋን ማድሪድን ጨምሮ ባርሴሎናንና ዛራጎዛን በመሳሰሉ ከተሞች በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ላይ ከፍተኛ ጭማሪ በመታየቱ መንግሥት ወረርሽኙ ለሁለተኛ ጊዜ ሊያገርሽ እንደሚችል እያስጠነቀቀ ነው።

የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴርም በሠራዊቱ ውስጥ ሊከሰት የሚችል ወረርሽኝን ለመለየትና ለመከላከል የሚያስችል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ሥርዓት ተግባራዊ እያደረገ ነው።

የጤና ሚኒስቴር ባለፈው አርብ ከ900 በላይ አዲስ ህሙማን መገኘታቸውን ያረጋገጠ ሲሆን፤ በሁለተኛ ዲቪዚዮን የሚጫወት አንድ የእግር ኳስ ቡድን 28 አባላቱ በበሽታው ተይዘውበታል።

ዩናይትድ ኪንግደም ከዛሬ ጀምሮ ከስፔን የሚመለሱ ሰዎች እራሳቸውን ለ14 ቀናት ለይተው እንዲቆዩ ያዘዘች ስታዝ፤ ኖርዌይም ተመሳሳይ እርምጃ እንደምትወስድ አሳውቃለች። ፈረንሳይ ደግሞ ወደ ስፔን ለሚደረጉ ጉዞዎች ማስጠንቀቂያ አውጥታለች።

ቤልጂየም ወደ ተወሰኑ የስፔን ግዛቶች የሚደረጉ ጉዞዎችን ስትከለክል፤ ዜጎቿ ወደ ሌሎች የስፔን ከተሞች ጉዞ እንዳያደርጉ እየመከረች ነው።

የስፔን ጤና ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ግን አገራቸው ውስጥ ያለው የወረርሽኙ ችግር በተወሰኑ ቦታዎች የተለየና በቁጥጥር ስር ያለ በመሆኑ ምንም የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

ከስፔን ባሻገር አውሮፓ ውስጥ ያሉ አገራት አዲስ በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን ለመቆጣጠርና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎችን መልሶ ለመክፈት ጥረት እያደረጉ ባሉበት ጊዜ በፈረንሳይና በጀርመን እየጨመረ የመጣ የህሙምን ቁጥር እየተመዘገበ ነው።

በአውሮፓ ውስጥ የታየው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር በሌሎችም አካባቢዎች ከታየው ጋር የሚያያዝ ሲሆን፤ ባለፉት ሁለት ቀናት በመላው ዓለም ከፍተኛ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ተመዝግቧል።

280 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ከተመዘገበ በኋላ "በዓለም ላይ በበሽታው ያልተጠቃ አገር ባይኖርም፤ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባላቸው የአህጉረ አሜሪካና የእስያ አገራት ውስጥ የታየው ጭማሪ ቁጥሩን ከፍ አድርጎታል" ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ከ15.7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከ640 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን ማጣታቸውን የጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ ያመለክታል።