ሰሜን ኮሪያ 'የመጀመሪያውን' የኮሮናቫይረስ ተጠርጣሪ ማግኘቷን አስታወቀች

ሰሜን ኮሪያ ውስጥ ሰው በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ጭምብል ማድረግ ግዴታ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሰሜን ኮሪያ ውስጥ ሰው በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ጭምብል ማድረግ ግዴታ ነው
ታትሟል

ሰሜን ኮሪያ በአገሪቱ የመጀመሪያው የተባለውን በኮሮናቫይረስ የተጠረጠረ ሰው ማግኘቷን አስታወቀች።

የአገሪቱ መንግሥት የዜና አገልግሎት እንደዘገበው በሽታው እንዳለበት የተጠረጠረው ግለሰብ ከሦስት ዓመት በፊት ወደ ደቡብ ኮሪያ ከድቶ ሄዶ የነበረ ሲሆን በቅርቡ በድንበር በኩል ወደ ሰሜን ኮሪያ ከተመለሰ በኋላ የወረርሽኙ ምልክቶች ታይተውበታል።

ይህንንም ተከትሎ የአገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ-ኡን ከፍተኛ በለስልጣኖቻቸውን ሰብስበው ከደቡብ ኮሪያ ጋር በምትዋሰነው የድንብር ከተማዋ ኬሶንግ ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲጣል ተደርጓል።

ለመረጃ ዝግ የሆነችው ሰሜን ቀደም ሲል በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው እንደሌለባት ስታሳውቅ ብትቆይም፤ ተንታኞች ግን ሊሆን አይችልም ሲሉ ቆይተዋል።

"በኬሶንግ ከተማ ድንገተኛ ነገር ተከስቷል፤ ከሦስት ዓመት በፊት ወደ ደቡብ ኮሪያ ኮብልሎ የነበረ ግለሰብ በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ተሻግሮ ወደ አገሪቱ ከገባ በኋላ ቫይረሱ እንዳለበት ተጠርጥሯል" ሲል የየአገሪቱ ዜና ወኪል ኬሲኤንኤ ዘግቧል።

ትናንት ቅዳሜ በተካሄደው የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት አስቸኳይ ስብሰባ መሪው ኪም ጆንግ-ኡን የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር "ከፍተኛ የአስቸኳይ ጊዜ ሥርዓት" እንዲዘረጋ አዘዋል።

በተጨማሪም ዜና ወኪሉ እንደዘገበው መሪው ኪም ጆንግ-ኡን በበሽታው የተጠረጠረው ግለሰብ በከፍተኛ ጥበቃ ስር ባለው የድንበር አካባቢ ከደቡብ ወደ ሰሜን ኮሪያ እንዴት አልፎ ሊገባ እንደቻለ እንዲመረመር ያዘዙ ሲሆን፤ ተጠያቂ የሚሆኑ ሰዎች ላይ "ከባድ የቅጣት እርምጃ" እንዲወሰድባቸው አዘዋል።

ነገር ግን ደቡብ ኮሪያ በተመሳሳይ ጊዜ ምንም አይነት ሕገ ወጥ የድንበር ማቋረጥ ክስተት እንዳልነበረ አሳውቃለች።

ከስድስት ወራት በፊት ቫይረሱ በዓለም ዙሪያ መስፋፋት በጀመረበት ጊዜ ሰሜን ኮሪያ ድንበሮቿን ዘግታ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ለይቶ ማቆያ ውስጥ አስገብታለች።

በዚህ ወር መጀመሪያ ገደማ ላይ መሪው ኪም ጆንግ-ኡን አገራቸው በኮሮናቫይረስ ላይ "አንጸባራቂ ስኬት" እንደተቀዳጀች አሳውቀው ነበር።