ትራምፕ ወደ ትላልቅ የአሜሪካ ከተሞች በመቶዎች የሚቆጠሩ የፌደራል ኃይሎችን ሊያዘምቱ ነው

የፌደራል ኤጀንቶች በፖርትላንድ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በርካታ የፌደራል የፀጥታና የደኅንነት ሠራተኞችን ወደ አሜሪካ ከተሞች በማሰማራት የተስፋፋውን ወንጀል ለመቀነስ እንደሚሰሩ ተናገሩ።

ቺካጎ እና ሌሎች ሁለት በዲሞክራቶች የሚመሩ ከተሞች ወንጀል በመጨመሩ የተነሳ በሪፐብሊካኑ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትኩረት ውስጥ ገብተዋል።

ነገር ግን በፖርትላንድ እና በኦሪጎን የፌደራሉ ፀጥታ አስከባሪ አካላት መሰማራታቸው አጨቃጫቂ መሆኑ ይታወሳል። የአካባቢው ባለስልጣናት እየተካሄደ ያለውን ህዝባዊ አመጽን ተከትሎ የፌደራል ፖሊሶቹ መገኘት ውጥረት ፈጥሯል ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዳግም ለመመረጥ በሚያደርጉት የምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ ካነሷቸው ቁልፍ ከሆኑ ሃሳቦች መካከል ሕግና ሥርዓት ማስከበር አንዱ ሆኗል።

በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ በሚኒያፖሊስ፣ ሚኒሶታ የጆርጅ ፍሎይድን ሞት ተከትሎ በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች ሕዝባዊ ተቃውሞ የተቀሰቀሰ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች የነበሩ ሰልፎች አመጽን የቀላቀሉ መሆናቸው ተስተውሏል።

ከዚህ መካከል እንደ ኒው ዮርክ፣ ፊላደልፊያ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ቺካጎ እና ሚልዋኪ ያሉ ከተሞች ውስጥ በመሳሪያ የታገዘ አመጽ ተስፋፍቷል።

በዚህም የተነሳ የአራት ዓመቱ ታዳጊ ሌጀንድ ታልፊሮ፣ በሰኔ ወር ካንሳስ ሲቲ በሚገኘው የቤተሰቦቹ ቤት ተኝቶ በነበረበት በወንጀለኞች ተገድሏል። የህጻኑ እናት ፕሬዝዳንቱ ረቡዕ እለት ባደረጉት ንግግር ላይ ከጎናቸው ቆማ ታይታለች።

በከተሞቹ የሚሰማሩት የፀጥታ አካላት ከፌደራል የወንጀል መከላከል ቢሮ (ኤፍቢአይ)፣ ከማርሻል ሰርቪስ፣ እና ሌሎች የፌደራል የጸጥታ ኃይሎች የተውጣጡ እንደሚሆኑ የአሜሪካ ፍትህ ቢሮ አስታውቋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለኮሮናቫይረስ በሰጡት ምላሽና በተጎዳው ምጣኔ ሃብት የተነሳ ተቀባይነታቸው እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም "የወንጀሎች መስፋፋት የዜጎችን ህሊና አስጨንቋል" ሲሉ ተደምጠዋል።

ፕሬዝዳንቱ ዲሞክራቶችን ወንጀልን በመከላከል ረገድ ደካማ ናቸው ሲሉ የተቹ ሲሆን፣ "በቅርብ ሳምንታት ውስጥ የፖሊስ ኃይሉን ለመከላከል፣ ለመበተን እና ለማፍረስ ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ ይኖራል" ብለዋል።

ለዚህም ጣታቸውን የቀሰሩት "አስደንጋጭ የሆኑ ተኩሶች፣ ግድያዎች፣ ሞት እና አስፀያፊ ወንጀሎች እና አመፆች" ላይ ነው።

"ደም መፍሰሱ መቆም አለበት" ያሉት ፕሬዝዳንቱ "የደም መፍሰሱ ይቆማል" ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው አረጋግጠዋል።

አክለውም "ፖለቲከኞች ከተማቸውንና አካባቢያቸውን ደኅንነት ለማረጋገጥ መደረግ ያለበትን ባለማድረጋቸው የተነሳ አንድም እናት የሞተ ልጇን ታቅፋ ማንባት የለባትም" ብለዋል።

የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ወደ ካንሳስ ሲቲ፣ ሚዙሪ 200 ያህል የፌደራል ኃይል አባላትን መላካቸውን ያረጋገጡ ሲሆን ወደ ቺካጎም ይህን ያህል ቁጥር ያለው ሠራዊት እንደሚያዘምቱ ገልፀዋል።

35 የፌደራል ጸጥታ ኃይል አባላት ደግሞ ወደ አልበከርኪ፤ ኒው ሜክሲኮ ይላካሉ ተብሏል።

ከ60 ሚሊየን ዶላር በላይ በአመጽ ለተጎዱ ከተሞች የፖሊስ መኮንኖችን ለመቅጠር በጀት ተይዟል።

የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃይሎች በፖርትላንድ ተሰማርተው ካከናወኑት "አመጾችንና የደቦ ጥቃቶችን" መከላከል በተለየ እነዚህ የፌደራል ኃይሎች "የታወቁ የወንጀል መከላከል" ሥራ ላይ ይሰራሉ ተብሏል።