የኢትዮጵያ አየር መንገድ እቃ ጫኝ አውሮፕላን በቆመበት በእሳት ተያያዘ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

አንድ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ እቃ ጫኝ አውሮፕላን ቻይና ውስጥ በቆመበት የእሳት አደጋ እንደገጠመው ተዘገበ።

ይህ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነ እቃ ጫኝ አውሮፕላን በቻይናዋ ሻንግሃይ ውስጥ በሚገኝ የአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ እቃ በሚጭነበት ወቅት ነው በእሳት መያያዙን አየር መንገዱ ያስታወቀው።

አየር መንገዱ ስለክስተቱ ባወጣው አጭር መግለጫ ላይ እንዳመለከተው አውሮፕላኑ ቦይንግ 777 የምዝገባ ቁጥሩ ET-ARH እቃ ጫኝ አውሮፕላን እንደሆነና እቃ በመጫን ላይ ሳለ በእሳት መያያዙን አረጋግጧል።

ጨምሮም በእሳቱ አደጋ ምክንያት በአውሮፕላኑ አብራሪዎችም ሆነ በየትኛው የአየር መንገዱ ሠራተኞች የደረሰባቸው ጉዳት አለመኖሩን የገለጸ ሲሆን፤ በአደጋው ሳቢያ በአውሮፕላኑ ላይ ስለደረሰው የጉዳት መጠን ግን ምንም የተገለጸ ነገር የለም።

በማኅበራዊ የመገናኛ መድረኮች ላይ የሚዘዋወሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንደሚያሳዩት የአውሮፕላኑ የኋለኛው ክፍል አቅራቢያ በእሳት ተያይዞ ሲነድና ጭስ ሲወጣ ይታያል።

አውሮፕላኑ ከሻንግሃይ በአዲስ አበባ በኩል ወደ ወደ ደቡብ አሜሪካዋ ሳኦፓሎ ከተማ መደበኛ የጭነት በረራ ለማድረግ ዝግጅት ላይ እንደነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባወጣው መግለጫ ላይ ተመልክቷል።

በተጨማሪም በአውሮፕላኑ ላይ የተከሰተው የእሳት አደጋ በቁጥጥር ሥር መዋሉና የእሳት አደጋው ምክንያትም እየተጣራ እንደሚገኝ አየር መንገዱ አስታውቋል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የአየር ትራንስፖርት ዘርፉ ክፉኛ በማዳከሙ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ የመንገደኛ አውሮፕላኖችን ወደ ጭነት አውሮፕላንነት በመቀየር የተለያዩ የጭነት አገልግሎቶችን በመስጠት በሥራቸው ላይ ከቀጠሉ ጥቂት የዓለማችን አየር መንገዶች አንዱ እንደሆነ ይነገራል።