ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አረብ ኤምሬቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ማርስ መንኮራኩር ላከች
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ማርስ መንኮራኩር (በእንግሊዘኛ ፕሮብ የሚባለውን) አስወንጭፋለች።
ከጃፓን የተነሳው ‘ሆፕ’ የተባለው ፕሮብ የማርስን የአየር ሁኔታ እና የአየር ጠባይ ያጠናል ተብሏል።
ይህን መንኮራኩር ባለፈው ሳምንት ሁለት ጊዜ ለማስወንጨፍ ተሞክሮ በአየር ሁኔታው ሳቢያ ሳይሳካ ቀርቶ ነበር።
‘ሆፕ’ ወይም ተስፋ የሚል ስያሜ የተሰጠው መንኮራኩር በቀጣዩ ዓመት ማርስ ይደርሳል። ይህም ከአረብ ኤምሬቶች ምስረታ የወርቅ ኢዮቤልዮ ጋር ይገጣጠማል።
የሮኬት ምርምሩ መሪ የሆኑት ክብርት ሳራ አል-አሚሪ፤ ሮኬቱን ሰማይ ላይ ሲያዩ ሀሴት ተሰምቷቸዋል። አሜሪካ ከ51 ዓመታት በፊት ‘አፖሎ 11’ ን ጨረቃ ላይ ስታሳርፍ የተፈጠረው አይነት ደስታ አገራቸው እንደተሰማትም ተናግረዋል።
“የኤሚሬቶች ልጆች ጠዋት ከእንቅልፋቸው የሚነሱት ትልቅ ህልም አንግበው ስለሚሆን ደስ ብሎኛል። በዓለም ላይ አሻራቸውን እንዲያኖሩም ያነሳሳቸዋል” ብለዋል።
ቻይና እና አሜሪካም በዚህ ወር ወደ ማርስ ሮኬት ያስወነጭፋሉ። መንኮራኩር ወደ ማርስ ለመላክ በዝግጅት ላይ የሚገኘው የአሜሪካ ቡድን፤ አረብ ኤምሬቶችን አንኳን ደስ አለሽ፤ ማርስ ላይ እስክንገናኝ በጉጉት እንጠብቃለን ብለዋል።
ኤምሬቶች ለምን ወደ ማርስ አቀናች?
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የህዋ መንኮራኩር በመሥራትና በማምረት ዘርፍ አምብዛም ልምድ የላትም። ሆኖም መንኮራኩር በማስወንጨፍ አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ አውሮፓ እና ሕንድን ተቀላቅላለች።
ኤምሬት መሀንዲሶች የሰለጠኑት በአሜሪካውያን ባለሙያዎች ነው። በስድስት ዓመታት ውስጥ ስኬታማ መንኮራኩር መገንባትም ችለዋል። ‘ሆፕ’ በማርስ ካረፈ በኋላ እስካሁን ስለ ፕላኔቷ ያልታወቁ ሳይንሳዊ መረጃዎችን ያቀብላል ተብሎ ይጠበቃል።
ሳይንቲስቶች በዋነኛነት የሚጠብቁት መረጃ፤ እንዴት ማርስ አብዛኛውን አየር እና የውሃ ክፍል እንዳጣች ነው።
መንኮራኩሩ መምጠቁ በአረብ አገራት ያሉ ታዳጊዎች ወደ ሳይንስ እንዲያዘነብሉ ያነሳሳል ተብሎ ይታመናል። የኤምሬት መንግሥት ነዳጅ ላይ ብቻ ከተመሰረተ ምጣኔ ሀብት እውቀትን ወደተመረኮዘ እድገት ለመሸጋገሩ አንዱ ማሳያም ነው።
በእርግጥ ማርስ ላይ ከተጀመሩ ጥናቶች ግማሾቹ ስኬታማ አልሆኑም። ይህንን የሚያውቁት የኤምሬት መንኮራኩር ፕሮጀክት ኃላፊ፤ “ምንም ቢሆን መሞከር አይከፋም” ይላሉ።
“ምርምሩ ላይሳካ ይችላል፤ ዋናው ከዚህ ፕሮጀክት ያገኘችው ጥቅም እና ትምህርት ነው” ብለዋል።
እንዴት ተሳካላት?
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግሥት የህዋ መንኮራኩሩን ከትልቅ የውጪ አገር መንግሥት መግዛት ስለማይችል በአገር ውስጥ መገንባት እንዳለበት ለፕሮጀክቱ ተሳታፊዎች ገልጾ ነበር።
ስለዚህም የኤምሬት ተወላጆች ከአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በጥምረት መሥራት ጀመሩ። ከአሜሪካ መሀንዲሶች በጋራ መንኮራኩሩን እንዲሁም ማርስን እንዲያጠኑ የተገጠሙለትን መሣሪያዎችም ገንብተዋል።
አብዛኛው የሳተላይት ግንባታ የተካሄደው በኮሎራዶ ዩኒቨርስቲ ሲሆን፤ የተቀረው ሥራ የተጠናቀቀው በዱባይ ነው።
የኮሎራዶ ዩኒቨርስቲ ከዚህ በኋላ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሙሉ በሙሉ በእራሷ አቅም ፕሮጀክት ማጠናቀቅ ትችላለች ብሏል።
‘ሆፕ’ ከማርስምንያገኛል?
ኤምሬት ‘ሆፕ’ የተሰኘውን ፕሮብ ያመጠቀችው እስካሁን ስለ ማርስ የተሠሩ ጥናቶችን ለመድገም አይደለም። ወደ አሜሪካው የህዋ ተቋም ናሳ ሄደው፤ እስካሁን በምርምር ያልተደረሰበት ምንድን ነው? ብለውም ጠይቀዋል።
የናሳ የማርስ ምርምር ዘርፍ፤ ‘ሆፕ’ ምን ማጥናት እንዳለበት ምክረ ሐሳብ ሰጥቷል። በዚህ መሠረትም፤ ማርስ ከባቢ አየር ላይ የግፊት ኃይል ቀኑን ሙሉ እንዲሁም ዓመቱን ሙሉ እንዴት ከታች ወደ ላይ እንደሚንቀሳቀስ ይጠናል።
በዚህ ፕሮጀክት፤ የማርስን ሙቀት የሚወስነው አቧራ ላይ ምርምር ይደረጋል።
በተጨማሪም ማርስ ላይ ስላለው የሀይድሮጅን አቶም እና ኦክስጅን ባህሪ ያጠናል።
የማርስ ከባቢ አየር እየተሸረሸረ የመጣው በእነዚህ አቶሞችና ከፀሐይ በሚፈነጥቀው ኃይል አማካይነት እንደሆነ መላ ምቶች አሉ። ይህም ማርስ ላይ የነበረው ውሃ ለምን እንደጠፋ ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል።
‘ሆፕ’ የሚሽከረከረው ከምድር ከ22,000 ኪሎ ሜትር እስከ 44,000 ኪሎ ሜትር ባለው ከፍታ ነው።