የኦሪጎን ግዛት ነዋሪዎቼን ከህግ ውጪ አስሯል በሚል የአሜሪካ ፌደራል መንግሥትን ከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኦሪጎን ግዛት ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለተቃውሞ የወጡ ሰልፈኞችን ያለ ህግ አግባብ አስሯል በሚል በፌደራል መንግሥቱ ላይ ክስ መስርቷል።
ጠቅላይ አቃቤ ህግ ኤለን ሮዘንብለም በአሜሪካ የፌደራል የፀጥታ፣ ደህንነትና ፖሊስ ቢሮዎች በሙሉ ተቃዋሚዎችን ከማሰር እንዲቆጠቡ ፍርድ ቤት ትእዛዝ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
"እንዲህ አይነት እርምጃዎች ሊቆሙ ይገባል" ያሉት ኤለን ሮዘንብለም "ዜጎች መብታቸውን እንዳያስከብሩና እንዲሁም በሰላማዊ ሁኔታ መቃወማቸውን የሚጥስ ነው። በጎዳናዎቻችንም ላይ ያልተረጋጋ ሁኔታ ይፈጥራል" ብለዋል።
የፌደራል ፀጥታ ኃይሎች እየወሰዱት ያለው እርምጃንም አውግዘዋል።
የትራምፕ አስተዳደር የፖርትላንድ ነዋሪዎችን ለማስፈራራት እየሞከሩ ነው በማለትም ወንጅለዋል። "ነዋሪዎች የፖሊስ ጭካኔንም ሆነ የብላክ ላይቭስ ማተር እንቅስቃሴን እንዳይደግፉም ጫና እያሳረፉ ነው" ያሉት አቃቤ ህጓ " ሁሉም አሜሪካዊ ሊጠየፈው የሚገባ ተግባር ነው፤ ይህ ተግባር በፖርትላንድ ከተከናወነ በሌሎችስ ላለመደረጉ ምን ዋስትና አለው" ብለዋል።
የጆርጅ ፍሎይድ በነጭ ፖሊስ መገደል ተከትሎ በፖርትላንድ የፖሊስ ጭካኔንና መዋቅራዊ ዘረኝነትን በመቃወም በርካቶች በምሽት ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ነበር።
ከሰሞኑም አርማ በሌለው መኪና የፌደራል ፖሊሶች መጥተው ተቃዋሚዎችን ከጎዳና ላይ በመውሰድ በቁጥጥር ስር ያዋሉዋቸው ሲሆን፤ ለምን እንዳሰሯቸውም ምክንያትም አልሰጡም።
ክሱም እንዲህ አይነት የማስፈራሪያ እርምጃዎች ዜጎች ከመንገድ ላይ ተወስደው አርማ በሌላቸው መኪናዎች በፌደራል ፖሊሶች መወሰዳቸው ህገ መንግሥታዊ የመሰብሰብ መብታቸውን የሚጥስ ነው ብለዋል።
ክሱ እንደሚያትተው የፌደራል ፖሊሶች በህገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረው 1ኛ፣ አራተኛና አምስተኛ አንቀፆችን ባለማክበር የዜጎቻቸውን መብት በመጣስ፣ ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ዜጎችን በማሰር እንዲሁም ሌሎች መብቶችን ጥሰዋል ይላል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የኦሪጎን ኃገረ ገዥ ኬት ብራውን ኃይል ያለ አግባብ በመጠቀም የፌደራል ፖሊሶችን ወቅሰዋቸዋል።
የፌደራል መንግሥት በበኩሉ የከተማዋን ሰላምና እርጋታ ወደቀደመ ለመመለስ ጥረት እያደረግኩ ነው ብሏል።
በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተሰማሩ የፌደራል ሰራዊት አስለቃሽ ጋዝ በመርጨት ሰልፈኞቹን ለመበተን ሞክረዋል። የአገሪቱ ፀጥታ መስሪያ ቤት ዋና ፀሐፊ ቻድ ወልፍ ተቃዋሚዎቹን "አመፀኛ ቡድን" በማለት ጠርተዋቸው ነበር።
በትናንትናው ዕለት ተቃዋሚዎች የፌደራል ፍርድ ቤቱ አካካቢ የሚገኝ አጥርን ሲገነጣጥሉ ነበር ተብሏል። በኦሪጎን የሚገኘው የጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ አጥሩ በተቃዋሚዎችና በፀጥታ ኃይሉ መካከል ያለውን ፍጥጫ ለመቀነስ በሚል አጥሩ እንደቆመ በትዊተር ገፁ አስታውቋል።












