ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ከመረጃ ፍሰት ይልቅ የሕዝባችንን ህይወት ማዳንን ቅድሚያ ሰጥተናል" ዛዲግ አብርሃ
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚኒስቴር ማዕረግ የዲሞክራሲ ግንባታ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ዛዲግ አብርሃ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከቢበሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ መንግሥት ከእርሱ ሃሳብ ጋር የማይስማሙትን እያሰረ እንዳልሆነ ተናገሩ።
ቢቢሲ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ ከሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በተፈጠረ አለመረጋጋት በቁጥጥር ስር የዋሉ ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችንና ወጣቶችን በመጥቀስ መንግሥት ከፖሊሲው ጋር የማይስማሙትን ማሰሩን ተጠይቀው መልስ ሰጥተዋል።
አቶ ዛዲግ በኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ያለውን ለውጥ በመጥቀስ በመንግሥትና በማኅበረሰቡ መካከል ያለውን ግንኙነት ለመቀየር መሰራቱን ያስታውሳሉ።
በአገሪቱ ባለፈው ሳምንት የተከሰተውን ሁከት በተመለከተም አሁን እየተደረገ ያለው ከፍተኛ የሆነ የሕግ ጥሰት ነው ያሉት አቶ ዛዲግ፣ በዚህም የተነሳ በርካታ ህይወት መጥፋቱን ጠቅሰዋል።
"መንግሥት ነገሮችን መቆጣጠር ይኖርበታል" በማለትም መንግሥት ሕግ እንዲያስከብር ከሕዝቡ ከፍተኛ ፍላጎት ነበር እኛም የሕግ ጥሰት የፈፀሙትን ላይ ነው እርምጃ የወሰድነው ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ ደግሞ የመንግሥት መሰረታዊ ዓላማ ነው በማለት መንግሥት እየወሰደ ያለው እርምጃ አግባብ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ዛዲግ አክለውም፣ መንግሥት እያለ ሕግ ካልተከበረ አስፈላጊነቱ ምን ላይ ነው ሲሉም ጠይቀዋል።
ከድምጻዊ ሃጫሉ መገደልን ተከትሎ በተነሳው አለመረጋጋት ከ200 በላይ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል። የእነዚህ ሰዎች ህይወት የጠፋው በጸጥታ አካል እርምጃ ነው ተብለው የተጠየቁት አቶ ዛዲግ የፀጥታ ኃይሉ ግጭት ወዳለበት ስፍራ ሲሰማራ እርምጃ ከመውሰድ ታቅቦ ነበር በማለት በዚህም የጸጥታ አባላት ጭምር ህይወት መጥፋቱን ተናግረዋል።
አለመረጋጋቱ በተከሰተበት ስፍራ የእርስ በእርስ ግጭት እንደነበር በማስታወስ የሰዎች ሞት ከዚህ ጋር የተያያዘ እንጂ በጸጥታ ኃይሉ አለመገደላቸው ተናግረዋል።
መንግሥት ለሁለት ቀን የነበረው ሁኔታ ተቆጣጥሮታል በማለትም፤ በድምጻዊው መገደል ስሜታቸውን የገለፁ ወጣቶች እንደነበሩ ገልፀው ከዚህ በተቃራኒው በብሔሮችና በሀይማኖቶች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሞከሩ መገናኛ ብዙሃን ስለነበሩ እርመጃ መወሰዱን ተናግረዋል።
መንግሥት የመገናኛ ቡዙሃንን መዝጋቱ የመናገር ነፃነትንን ማፈን እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ዛዲግ አሁንም የአገሪቱን ሕግ አክብረው እየሰሩ ያሉ መገናኛ ብዙሃን በሥራ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።
አክለውም መንግሥት ከዚህ ቀደም ታስረው የነበሩ እስረኞችን መፍታቱን በመጥቀስ የመናገር ነጻነትን የማፈን ፍላጎት እንደሌለው አብራርተዋል።
"የመናገር ነጻነት ፍፁም መብት አይደለም" በማለትም እነዚህ መገናኛ ብዙሃን በብሔሮች መካከል ግጭቶች ለመቀስቀስ መሞከራቸውን ተናግረዋል።
"ያ ደግሞ እንዲሆን አንፈቅድም" በማለት "ለሰው ልጆች ሕይወት ቅድሚያ መስጠት አለብን" ብለዋል።
በእነዚህ መገናኛ ብዙሃን ቅስቃሳ ህይወቶች መጥፋታቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ይህም የሚያያዘው መገናኛ ብዙሃንን ከመዝጋት ጋር ሳይሆን የአገሪቱ ሕግ ከመከበሩ ጋር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ዛዲግ አሁንም ከመንግሥት ሃሳብ በተቃራነው የቆሙ መገናኛ ብዙሃን አሉ ካሉ በኋላ እነርሱ ግን የአገሪቱን ሕግ አክብረው እየሰሩ በመሆናቸው አልተዘጉም በማለት ስርጭታቸው የተቋረጠው አንድ እና ሁለት ብቻ ናቸው ሲሉ አብራርተዋል።
ኢንተርኔትን ስመዘጋቱ የተጠየቁት አቶ ዛዲግ፣ ይህ ደግሞ ዜጎች መረጃ የማግኘት መብታቸውን ማፈን መሆኑን በማስመልከት ሲጠየቁ ኢንተርኔት ለጥላቻ ንግግር ማሰራጫ መሳሪያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢንተርኔት በብሔሮችና በሐይማኖቶች መካከል ግጭቶች እንዲቀሰቀስ መሳሪያ በመሆን ማገልገሉን የሚናገሩት የዲሞክራሲ ግንባታ ሚኒስትሩ፤ መምረጥ የነበረብን ከመረጃ ነጻ ፍሰትንና የሕዝባችን ህይወት መካከል ነበር ያሉት አቶ ዛዲግ ለሰው ልጅ ሕይወት ቅድሚያ ሰጥተናል ብለዋል።
የሕዝቦች አብሮ የመኖር ባህልን አደጋ ላይ ጥሏል ያሉት በኢንተርኔት የሚሰራጭ የጥላቻ ንግግር "ሁሉንም ነገር ስንቆጣጣር ይመለሳል" ሲሉም አስታውቀዋል።
በአገሪቱ ውስጥ በተከሰተው አለመረጋጋት ውስጥ የውጪ ኃይሎች መሳተፋቸውን በተመለከተ መንግሥት እርግጠኛ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዛዲግ ማን ነው የሚለው ላይ ግን አሁን ለመናገር ጊዜው ገና ነው በማለት ምርመራው እስኪጠናቀቅ መጠበቅ አለብን ብለዋል።