የመብት ድርጅቱ ቡርኪና ፋሶ ውስጥ የ180 ሰዎች ሬሳ አግኝቻለሁ ይላል

ታትሟል

በሰሜናዊ ቡርኪና ፋሶ ታጣቂዎችና ወታደሮች የሚፋለሙበት ሥፍራ ላይ አንድ የጅምላ መቃብር ውስጥ የ180 ሰዎች ሬሳ መገኘቱን ሂዩማን ራይትስ ዎች የተሰኘው ተቋም ይፋ አድርጓል።

የድርጅቱ ሪፖርት እንደሚጠቁመው "በጅምላ ግድያው የመንግሥት ወታደሮች እጅ ሳይኖርበት አይቀርም።"

የመብት ተከራካሪው ድርጅት ሬሳዎች በሃያ ሃያ እየሆነ በሰባት ወራት ውስጥ ጂቦ የተሰኘች ከተማ ካለ አንድ የጅምላ መቃብር ውስጥ ተጥሏል ይላል።

የቡርኪና ፋሶ መከላከያ ሚኒስትር ታጣቂዎች ከክስተቱ ጀርባ ናቸው ሲሉ ይወቅሳሉ።

«ሕዝቡ የታጠቁ አሸባሪዎችንና የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎችን ለይቶ ላያውቅ ይችላል» ይላሉ ሚኒስትር ቸሪፍ ሞሚና ሳይ ለድርጅቱ ረፖርት ምላሽ ሲሰጡ። ሚኒስትሩ አክለው መንግሥት ጉዳዩን ያጣራል ብለዋል።

'የግድያ አውድማ'

በየብስ የታጠረችው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር ቡርኪና ፋሶ ከአል-ቃኢዳ እንዲሁም ኢስላሚክ ስቴት ከተሰኙት ቡድኖች ጋር ግንኙነት ያላቸውን እስላማዊ ታጣቂዎች ስትፋለም ዓመታት ተቆጥረዋል።

የሂዩማን ራይትስ ዎች የሳህል ቀጣና ኃላፊ የሆኑት ኮሪን ዱፍካ፤ ጂቦ የተሰኘችው ከተማ 'የግድያ አውድማ' ሆናለች ይላሉ።

ቡድኑ የቡርኪና ፋሶ መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት እርዳታ ሊያገኝ ይገባል ይላል። አልፎም የሬሳዎቹ ማንነት ተረጋግጦ አፅማቸው ለቤተሰቦቻቸው ሊመለስ ይገባል ይላል።

የድርጅቱ አጥኚዎች ጂቦ ከተማ የሚገኙ 23 ሰዎችን አናግረዋል። ገበሬዎች፣ ነጋዴዎች፣ አርብቶ አደሮች፣ የመንግሥት ሠራተኞችና የእርዳታ ሠራተኞች እንደሚገኙበት ተነግሯል። ቃለ-ምልልስ የተደረገላቸው ነዋሪዎች የመንግሥት ኃይሎች ታጣቂ ናቸው ብለው የጠረጠሯቸውን ሰዎች ገድለዋል ይላሉ።

በሳህል ቀጣና የፀጥታ ስጋት መስፈን የጀመረው እስላማዊ ታጣቂዎች ሰሜናዊ ማሊን መቆጣጠር ከጀመሩ ወዲህ ነው። ፈረንሳይ በስፋራው ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ከጀመረች ዓመታት አልፏታል።

ከማሊ የተነሱት ታጣቂዎች ወደ ቡርኪና ፋሶ እና ጂጀር በመስፋፋት የቀጣናውን ሰላም ያናጉት ከፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ ነው።