ኮሮናቫይረስ፡ በበይነመረብ የሚማሩ የውጭ አገር ተማሪዎች ከአሜሪካ እንዲወጡ መወሰኑ ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ስርጭት ለመግታት በሚል የተለያዩ የትምህርት ተቋማት በአካል ማስተማርን በበይነ መረብ ወደሚደረግ አማራጭ የትምህርት ስርአት ተክተውታል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በአሜሪካ ውስጥ በተማሪ ቪዛ ያሉ የውጭ አገር ተማሪዎች አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ ተወስኗል።
የውጭ አገራት ዜጎችን በተመለከተ በበላይነት የሚመራው የመንግሥት ተቋም አይስ (ኢሚግሬሽን ኤንድ ከስተምስ ኢንፎርስመንት) ተማሪዎቹ በበይነ መረብ ብቻ የሚማሩ ከሆነ ከአገር እንዲወጡ እንደሚደረግም አስታውቋል። ያላቸው አማራጭም የሚማሩባቸውን ተቋማት በመቀየር በአካል ትምህርት የሚወስዱበትን መንገድ ማመቻቸት አለባቸው ተብሏል።
በርካታ የአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ሆኖ ከመቀጠሉም ጋር ተያይዞ በሚቀጥለው አመትም ቢሆን ትምህርትን በበይነ መረብ ለማካሄድም እያሰቡ ነው።
በዚህም የተነሳ ምን ያህል ተማሪዎች ተፅእኖ ውስጥ እንደሚወድቁ ቁጥሩ አልተጠቀሰም። ለጊዜው በጊዜያዊነት ወደበይነ መረብ ትምህርት ያሸጋገሩ ተቋማት ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎችና ለአጭር ጊዜ ትምህርት በአሜሪካ ውስጥ ያሉ ተማሪዎች በአገሪቷ ውስጥ እንዲቆዩና እንዲያጠናቅቁ ይደረጋል።
ይሄ ሁኔታ ግን ለሚቀጥለው አመት የትምህርት ወቅት ተግባራዊ አይሆንም። ውሳኔውም ኤፍ 1ና ኤም1 የተሰኙ ቪዛ ያላቸውን ተማሪዎች እንደሚመለከትም ከአይስ መግለጫ መረዳት ይቻላል።
ከሰሞኑ ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ለሚቀጥለው አመት ትምህርት በበይነ መረብ እንደሚሆን አሳውቋል። በግቢው ማደሪያ ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎችም ቢሆኑ በበይነ መረብ እንዲማሩ ተወስኗል።
ክሮኒክል ኦፍ ሃየር ኤዱኬሽን ከተባለው ድርጅት በተገኘው መረጃ 9 በመቶ የሚሆኑት ዩኒቨርስቲዎች በመጪው በጋ ትምህርቶቻቸውን በበይነ መረብ ለማካሄድ እንደወሰኑ ነው። ሁኔታው ግን በሚቀጥሉት ወራት ሊቀየር ይችላል።
የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ላሪ ባኮው ባወጡት መግለጫም አይስ ያወጣውንም መመሪያ ተቃውመውታል።
ከዚህም በተጨማሪ የዲሞክራቷ ሴናተርም ኤልዛቤት ዋረን "ዩኒቨርስቲዎች በበይነ መረብ በማስተማራቸው ምክንያት ተማሪዎችን ከአሜሪካ ማስወጣት ጨካኝነት፣ ትርጉም የሌለውና ፀረ-የውጭ አገር ዜጎች ነው" ብለዋል
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ

በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደርን ጨምሮ በርካታዎች ይህንን ውሳኔ ያወገዙት ሲሆን በተለያዩ ሃገራት ያሉትን ሁኔታዎች እንዲሁም በአገራት መካከል ያለውን የሰዓት ልዩነት ያላጤነ ነው ብለውታል።
በሳውዝ ፍሎሪዻ ዩኒቨርስቲ የድህረ ምረቃ ትምህርቱን እየተከታተለ ያለው ፓኪስታናዊው ሙሃመድ ኤሃብ ራሱል ውሳኔው ለአለም አቀፍ ተማሪዎች አስደንጋጭ ነው ብሏል።
"እንደ አለም አቀፍ ተማሪነታችንና በአገሪቷ ውስጥም አናሳ እንደመሆናችን መጠን አሜሪካ ውስጥ ለመቆየት ሁሌም ምክንያት አቅርቡ መባል አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት ጉዳይ ነው። በዩኒቨርስቲው ትምህርታችንን ለመጪው አመታት እንከታተል አንከታተል እንኳን አናውቅም፤ ይሔ አሳሳቢ ነው" ብሏል።














