ኮሮናቫይረስ: የብራዚሉ ፕሬዝዳንት በኮቪድ-19 መያዛቸው ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የብራዚል ፕሬዝዳንት ጃየር ቦልሶናሮ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተገለፀ።
ፕሬዝዳንቱ ኮሮናቫይረስ በአገራቸው ከተከሰተ ጀምሮ ለአራተኛ ጊዜ ምርመራ ማድረጋቸው የተገለፀ ሲሆን፣ ሰኞ እለት ያደረጉት የአሁኑ ምርመራ ግን የሙቀት መጠናቸው ከፍ በማለቱና የኮሮናቫይረስ ምልክት በማሳየታቸው መካሄዱ ተገልጿል።
ቦልሶናሮ በተደጋጋሚ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሚከሰቱ የጤና አደጋዎችንና ቀውሶችን ሲያጣጥሉ የነበረ ሲሆን፣ " ቀላል ጉንፋን" በማለት ቢያዙ በጣም ሊጎዱ እንደማይችሉ ሲናገሩ ተደምጠው ነበር።
ፕሬዝዳንቱ የክልል አስተዳዳሪዎችንም የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት ጥለውት የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲያነሱ ተናግረው የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱም የእንቅስቃሴ ገደቡ ምጣኔ ሃብትን ይጎዳል ብለው ነበር።
ሰኞ እለትም በአፍና በአፍንጫ መሸፈኛ ላይ የተላለፈውን መመሪያ አጣጥለውት ሲናገሩ ተደምጠዋል።
በሚያዚያ ወርም በቫይረሱ ቢያዙ እንኳ" አያስጨንቀኝም ቢሆን ቢሆን መጠነኛ ጉንፋን ነው" በማለት ተናግረው ነበር።
ይህንን አስተያየት በሰጡበት ወቅት በኮቪድ-19 ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ3000 በታች የነበረ ሲሆን በቫይሩሱ የተያዙትም 40 ሺህ ብቻ ነበር።
በብራዚል በአሁኑ ወቅት በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ65 ሺህ በላይ ሲሆን በቫይረሱ የተያዙም ከ1.6 ሚሊዮን በላይ ደርሰዋል።
ምንም እንኳ በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ቢመጣም፣ ፕሬዝዳንቱ ግን የክልል አስተዳደሮች የጣሉት የእንቅስቃሴ ገደብ ምጣኔ ሃብቱን ከቫይረሱ በላይ እየጎዳው እንደሆነ ተናግረው፣ መገናኛ ብዙኀንም ስለቫይረሱ ፍርሃትና ውዥንብር እየነዙ ነው ሲሉ ኮንነዋል።
ፕሬዝዳንቱ ሰኞ እለት ብራዚላውያን ህዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ የሚደነግገውን ህግ መጠነኛ ለውጥ አድርገውበታል።
ቦልሳኖሮ በተደጋጋሚ ህዝብ በበዛበት ስፍራ ሲገኙ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ ታይተዋል።
በብራዚል የአሜሪካ አምባሳደር፣ በአሜሪካ የነጻነትን ቀንን አስመልክቶ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮን ጋብዘው ነበር።
በዚህም የተነሳ የፕሬዝዳንቱ በኮቪድ-19 መያዝን አስመልክቶ ምርመራ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
ቅዳሜ እለት ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ጋር የአሜሪካውን አምባሳደር ቶድ ቻፕማንንን አቅፈው የአሜሪካ የነጻነት በዓልን ሲያከብሩ የተነሱት ምሰል በትዊትር ላይ ታይቷል።
ፕሬዝዳንቱ በቫይረሱ መያዛቸው እንደተሰማ ኤምባሲው በትዊትር ላይ አምባሳደሩ "ምልክት አልታየባቸውም ነገር ግን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ ያደርጋሉ" የሚል መልእክት አስፍሯል።
የአሜሪካ ኤምባሲ መልእክት አክሎም ምርመራ እንደሚያደርጉ ገልጾ" የምርመራ አሰራሮችን ይከተላሉ" ብሏል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
ፕሬዝዳንቱ የኮሮናቫይረረስ ምርመራ ሲያደርጉ የመጀመሪያ ጊዜያቸው አይደለም፤ ከዚህ በፊት ሶስት ጊዜ ተመርምረው የሚያውቁ ሲሆን ሁሉም ነጻ መሆናችን የሚያሳዩ ነበር ተብሏል።














