ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አስራ ስምንት ሆስፒታሎች አናክምም ብለው የመለሱት ህንዳዊ በኮሮናቫይረስ መሞቱ ድንጋጤን ፈጠረ
በህንዷ ደቡባዊ ግዛት ባንጋሎር የሚገኙ ሆስፒታሎች ህክምና የከለከሉት ግለሰብ በኮሮናቫይረስ መሞቱን ተከትሎ መንግሥት በዘጠኙ ላይ ምርመራ መጀመሩን የቢቢሲ ሂንዲ ዘጋቢ ኢምራን ቆረሺ ዘግቧል።
የአምሳ ሁለት አመቱ ባሃዋርላል የመጨረሻ ህቅታውም የወጣችው አናክምም ካሉት ሆስፒታሎች በአንደኛው በር ነው።
ህክምና እንዲያገኝ የለፋለት ወንድሙ ዲኔሽ ሱጃኒ የወንድሙን የመጨረሻ ሰዓታትም በማስታወስ ሲያነባ እንዲሁም ኃዘኑን መቆጣጠርም አቅቶት ታይቷል።
የኮሮናቫይረስ ምልክት ባሃዋርላል ማሳየት በጀመረበት ወቅት ወንድሙ በባጃጅ ብሃግዋን ማሃቪር ሆስፒታል ይዞት ከነፈ። ሆስፒታሉም የሚገኘው ከቤታቸው በአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ነው።
"መተንፈስ እንደከበደውና እያስመለሰውም እንደሆነና የትንፋሹ መጠንም እየቀነሰ እንደሆነ ነገርኳቸው" ይላል ወንድሙ ዲኔሽ
"ወደ ውስጥ አስገቡትና ኤክስሬይ አነሱት ከዚያም ወጡና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተፃፈ ወረቀት ይዘው ከዚህ እንድወስደው ነገሩኝ"ይላል
ሆስፒታሉም ሆነ ሰራተኞቹ ህክምና ለብሃዋርላል ህክምና ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበሩም።
ወንድሙ ዲኔሽ አምቡላንስ አግኝቶ ወደ ሌላ ሆስፒታል ለህክምና ቢወስደውም በእዚህም ሆስፒታል በተመሳሳይ መልኩ ሊያክሙት ፈቃደኛ አልሆኑም።
ወንድማማቾቹ ከሆስፒታል ወደ ሆስፒታል ህክምና ለማግኘት ቢሯሯጡም እደል አልቀናቸውም። የመንግሥትም ይሁን የግል ሆስፒታሎች ወንድሙን አናክምም እንዳሉ የሚናገረው ዲኔሽ "አንዳንዶቹማ ከበር መልሰውናል" ብሏል።
የባሃዋርላል የመጨረሻ ልጅ ቪክራም ለሃገሪቱ ሚዲያ እንደተናገረው "አስራ ስምንት ሆስፒታሎች በአካል በመሄድ ጠይቀናል፤ 32 ጋር ደግሞ ደውለናል። 120 ኪሎሜትር ርቀትም ተጉዘናል።የትኛውም ሆስፒታል አባቴን ለማከም ፈቃደኛ አይደሉም ብሏል።
የአባቱ ታሪክ በህንድ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ታመው ህክምና ተከልክለው ከሞቱ ሰዎች መካከል አንዱ ነው።
በርካታ ሚዲያዎች እንደዘገቡት የኮሮናቫይረስ ምልክት የሚያሳዩ ሰዎች በተለያዩ ሆስፒታሎች ህክምና ተከልክለው እንደሞቱ ነው። የባንጋሎር መዲና የሆነችው ካርናታካ ግዛትም አንድ የመንግሥት ሆስፒታልን ጨምሮ ዘጠኝ ሆስፒታሎች በባህዋርላል ሞት ተጠያቂ ለምን እንደማይሆኑ ምክንያታቸውን እንዲያስረዱ ደብዳቤ ፅፏል። ክስም ሊመሰረትባቸው ይችላል እየተባለ ነው።
የግል የጤና ተቋማትም ቢሆኑ የኮሮናቫይረስ ምልክትን የሚያሳዩም ሆነ ህሙማኑንም ለመከልከል እንደማይችሉ የሃገሪቱ የጤና ኮሚሽነር ፓንካጅ ኩማር ባንዴይ በፃፉት መግለጫ አስታውቀዋል።
ነገር ግን ሆስፒታሎች ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ እየተናገሩ ነው። ባህዋርላል መጀመሪያ ለህክምና የተወሰደበት ሆስፒታል ብሃግዋን ማሃቪር ዶክተር የሆኑት ዶክተር ኒሻንት ሃየርማዝ እንደተናገሩት ለኮሮናቫይረስ ህሙማን ተብለው የተመደቡት አርባ አምስት አልጋዎች በወቅቱ ተይዘው ነበር ብለዋል።
ዶክተሩ የ ባሃዋርላል ቤተሰቦች ሆስፒታሉ ህክምና ሊሰጠን ፈቃደኛ አልሆነም ማለታቸውን አይቀበሉትም። ለህመምተኛው ኦክስጅንን ጨምሮ የመጀመሪያ ህክምና እንዳደረጉለት ይናገራሉ።
"የመንግሥት ሆስፒታል እንዲወስዱት ምክር ለግሰናቸዋል። እንዲሁም የምራቅ ናሙናውን እንዲመረመር እንዲያደርጉም" ነግረናቸዋል ይላሉ።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በቅርቡ በከፍተኛ ሁኔታ በግዛቷ ማሻቀቡ ለጤና ማዕከላቱ ችግር ሆኗል ተብሏል። ካርናታካ ግዛት የኮሮናቫይረስ ህሙማን ጋር ግንኙነት እንዲሁም የታወቀ ንክኪ ያላቸውን ግለሰቦች ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ የስርጭቱ ማዕከል ከሆኑት ደልሂ፣ ማሃራሽትራና የመሳሰሉት ግዛቶች ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ስራ በመስራቷ ምስጋና ተችሯታል።
ነገር ግን ለሶስት ወራት የቆየው አስገዳጅ የቤት መቀመጥ መመሪያ መነሳቱን ተከትሎ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አሻቅቧል ተብሏል።
በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ በግዛቷ 308 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 64 ሞትም ተከስቷል። በዚህ በያዝነው ሳምንት ግን 1 ሺህ 272 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋጋጠ ሲሆን የሟቾችም ቁጥር 253 ደርሷል። በዚሁ ወቅት በባንጋሎር ብቻ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከ18 ወደ 732 ማሻቀቡም ተነግሯል።
የመንግሥት ባለስልጣናት የጤና ማዕከላቱን አቅም ለመጨመር እየሰሩ ነው። በሃገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ የግል ሆስፒታሎችም ጋር ስምምነት በመፍጠር ለኮሮናቫይረስ ህሙማን እንዲሆኑ አልጋ የማስለቀቅ ስራ በሚቀጥሉት ቀናት ይጠናቀቃልም ተብሏል።
"መንግሥት ከ7ሺህ አስከ 7ሺህ 500 የሚጠጉ አልጋዎች ከግል የጤና ዘርፉ ያገኛል። ይህም ማለት ለሚቀጥለው ወር ዝግጁ ሆነን እንጠብቃለን" በማለት የካርናታካ የጤና ማህበር ፌደሬሽን ዋና አስተባባሪ ዶክተር ኤምሲ ናጌንድራ ስዋሚ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በግዛቷ ለሚገኘው 64 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብም አስር ሺህ አልጋም አለ ተብሏል።
ነገር ግን የጤና ባለሙያዎች በትንሽ ቁጥር አልጋዎችን መጨመር ፍሬያማ እንዳልሆነ ነው። ምክንያቱም በሐምሌና ነሃሴ ወራት የወረርሽኙ ጣራ የሚነካበት ጊዜም ነው ተብሏል።