በሕንድ አንዲት ግዛት የውሻ ሥጋን መሸጥና መመገብ ከለከለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሕንዷ ናጋላንድ ግዛት የውሻ ሥጋ ወደ ግዛቲቱ ማስገባትና መሸጭ መከልከሏን ተከትሎ በርካታ የእንስሳት መብት ተሟጋቾች ደስታቸው እየገለጹ ይገኛሉ።
በሰሜን ምሥራቅ ሕንድ የምትገኘው ግዛት አስተዳደር ውሳኔውን ያስተላለፈው በርካታ ድርጅቶች ለዓመታት ሲያቀርቡት የነበረውን ተቃውሞ ተከትሎ ነው።
የእንስሳት መብት ተሟጋች ድርጅቶቹ ውሳኔውን በሕንድ ውስጥ በውሾ ላይ ለሚፈጸሙ ጭካኔዎች ማብቃት "ትልቅ ጅማሬ" ነው በማለት አሞካሽተውታል።
ነገር ግን የመንግሥትን ውሳኔ የተቹ አልጠፉም። መንግሥት እንዴት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምግቦች ላይ እገዳ ይጥላል? በማለትም ተከራክረዋል።
ምንም እንኳን በአንዳንድ የሕንድ ግዛቶች የውሻ ሥጋን መመገብ ክልክል ቢሆንም በሰሜን ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ አካባቢዎች ግን የውሻ ሥጋ እንደ ልዩ ምግብ አይነት ነው የሚቆጠረው።
መንግሥት ውሳኔውን እንዴት እንደሚያስፈጽም እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
የሕንድ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከሰሞኑ ጭቃማ የሆነ ገበያ ውስጥ በርካታ ውሾች በአንድ ቅርጫት ታጭቀው የሚያሳይ ምስል በማኅበራዊ ሚዲያ መሰራጨቱን ተከትሎ እንደሆነ ዘግበዋል።
ባሳለፍነው ሐሙስ ደግሞ የሕንድ እንስሳት ጥበቃ ፌደሬሽን በተመለከተው ነገር በእጅጉ ማዘኑንና ውሾቹ በእንዲህ አይነት አስደንጋጭ ሁኔታ መያዛቸው ሳያንስ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለው ሥጋቸው ለምግብነት መዋሉ እንጅ ዘግናኝ ነው ብሏል።
ፌደሬሽኑ አክሎም መንግሥት በአፋጣኝ የውሻ ሥጋ ንግድን እንዲከለክል ጠይቋል።
ይህን ፌደሬሽን ጨምሮ በሕንድ ለእንስሳት መብት የሚከራከሩ በርካታ ድርጅቶች በናጋላንድ ያለው የውሻ ገበያ እንዲዘጋና ውሾች ለምግብነት መዋል እንዲያቆሙ ለዓመታት መንግሥትን ሲወተውቱ ቆይተዋል።
በዓመት ቢያንስ እስከ 300 ሺህ የሚደርሱ ውሾች በሕገወጥ መንገድ ወደ ናጋላንድ የሚገቡ ሲሆን ክፍት ገበያ ውስጥ ከተሸጡ በኋላ በዱላ ተደብድበው ይገደላሉ። ከዚያ ነው ሥጋቸው ለምግብነት የሚውለው።
በያዝነው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ሌላኛዋ የሕንድ ግዛት ሚዞራም የውሻ ሥጋ ንግድ እንዲቆም ከልክላለች።
ከሕንድ በተጨማሪ የውሻ ሥጋን እንደ ልዩ ምግብ ቆጥረው የሚመገቡ ሰዎች ከሚገኙባቸው አገራት መካከል ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ እና ታይላንድ ይጠቀሳሉ።












