ፕሬዝደንት ትራምፕ ሐውልቶች ላይ ጥቃት የሚያፈጽሙ 'አመፀኞች' ዘብጥያ ይወርዱ እያሉ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ታሪካዊ ሐውልቶች ላይ ጥቃት የሚደርሱ ተቃዋሚዎችን ማሠር የሚያችል አንቀፅ ያለው ትዕዛዝ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።
ትዕዛዙ እንደሚለው አደባባይ የቆመን ማንኛውም ሐውልት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ሰው በሕግ ይጠየቃል፤ ለእሥርም ይዳረጋል።
አልፎም ትዕዛዙ 'የደቦ ጥቃት' የሚያደርሱ ሰዎችን ይዘው ማሰር ያልቻሉ የሕግ አስፈፃሚ አካላት ከፌዴራል መንግሥት ፈንድ ይነፈጋቸዋል የሚል ትዕዛዝ ፕሬዝደንቱ አስተላልፈዋል።
ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ ከተገደለ በኋላ አሜሪካው ውስጥ የተቀጣጠለውን ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ሐውልቶች ከጥቅም ውጪ መሆናቸው አይዘነጋም።
አርብ ዕለት ትዕዛዙን ያስተላለፉት ፕሬዝደንቱ ኒው ጀርሲ ወደሚገኘው የጎልፍ መጫወቻ ሜዳቸው ይሄዳሉ ተብሎ ሲጠበቅ ነበር። ፕሬዝደንቱ የጎልፍ ጨዋታ ክፍለ ፕሮግራማቸውን ሰርዘው ዋሽንግተን በመቆየት 'ሕግና ሥርዓት ለማስጠበቅ' መወሰናቸውን ያስታወቁት በትዊተር ግድግዳቸው ላይ በፃፉት መልዕክት ነው።
«ይህንን ድርጊት የፈፀሙ በርካታ አመፀኞች፣ ታጣቂዎች እንዲሁም ግራ ዘመመ አክራሪዎች ድርጊታቸውን ከተለያዩ ርዕዮተ ዓለሞች ጋር እያቆራኙ ነው። ከእነዚህ አንዱ ደግሞ ለዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ጥፋት የሚመኘው ማርክሲዝም ነው።»
ትዕዛዙ የተላለፈበት ደብዳቤ ተቃዋሚዎቹን 'ለታሪካችን ቦታ የማይሰጡ' ሲል ይወቅሳቸዋል።
በቅርቡ ሳን ፍራንሲስኮ ውስጥ የሚገኘው የኡሊሴስ ግራንት ሐውልት ከጥቅም ውጭ መሆኑ ይታወሳል። ግራንት የዩኒየን ሠራዊት አዛዥ ሆኖ በአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ባርነትን ደግፈው የተዋጉ ኃይሎችን ከመርታቱ በፊት ባርነትን ይደግፍ ነበር። ትዕዛዙ የዚህ ግለሰብ ሐውልት መፍረሱ ተገቢ አይደለም ይላል።
ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ሐውልት እንዲፈርስ በሰላማዊ መንገድ መጠየቅ ይችላሉ፤ ነገር ግን ማንም ሰው ሐውልት የማፍረስ ወይም ጉዳት የማድረስ መብት የለውም ሲል ትዕዛዙ ያስጠነቅቃል።
የሕዝብ ንብረት ያወደመ ሰው እስከ 10 ዓመት ድረስ ሊቀጣ ይችላል የሚለውን ሕግ ትዕዛዙ አጣቅሷል።
የግዛቶች ፖሊሶች ይህንን ሕግ ማስፈፀም ካልቻሉ ከፌዴራል መንግሥት የሚመደብላቸው በጀት ሊቀር ይችላል ሲል የዶናልድ ትራምፕ አዲሱ ትዕዛዝ ያትታል።
አሜሪካ ውስጥ በተለይ ደግሞ የባሪያ ንግድን ይደግፉ ከነበሩት ኮንፌዴሬቶች ጋር ግንኙነት ያላቸው ሐውልቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተቃወሚዎች ጉዳት እየደረሰባቸው ነው።
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የኮንፌዴሬት ሠራዊት የአሜሪካ ታሪክ አካል ነው ማለታቸው አይዘነጋም።
በ15ኛው ክፍለ ዘመን ከአውሮፓ ተነስቶ አሜሪካ የደረሰው የአሳሹ ክርስቶፈር ኮሎምበስ ሐውልቶችም ብዙ ጊዜ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ብዙዎች ኮለምበስ አውሮፓውያን ኢምፔሪያሊስቶች ክፈለ አሜሪካን ቅኝ እንዲገዙ መንገድ ከፍቷል ሲሉ ይተቻሉ።
አንዳንድ ግዛቶች እና ከተማዎች የኮንፌዴሬት አባላት ሐውልቶች እንዲወገዱ ትዕዛዝ እየሰጡ ነው።












