በአዲስ አበባ ሁለት ህጻናትን የደፈረው የ64 ዓመቱ ግለሰብ 60 ዓመት ተፈረደበት

ካቴና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

አዲስ አበባ ውስጥ በአቃቂ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነ የ64 ዓመት ግለሰብ ዕድሜያቸው ስምንትና ዘጠኝ ዓመት የሆኑ ሁለት ሴት ህጻናትን በመድፈሩ የ60 ዓመት እስር ተፈረደበት።

ግለሰቡ በተለያዩ ቀናቶች ተከራይቶ ወደሚኖርበት ቤት ሁለቱን ታዳጊዎች በመውሰድ አስገድዶ በመድፈሩ ነው ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት ብይኑን ያስተላለፈው።

በዚህም ፍርድ ቤቱ ግለሰቡ ለፈጸመው ወንጀል በ60 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የፈረደበት ቢሆንም የተከሰሰበት ድንጋጌ የቅጣት ጣሪያው 25 ዓመት በመሆኑ 25 ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፍ ተወስኖበታል፡፡

አቃቤ ሕግ እንዳለው ተከሳሹ የቀረበበትን ክስ እንዳልፈጸመ ክዶ ቢከራከርም ድርጊቱን መፈጸሙን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች በማቅረባቸው ከቅጣቱ አላመለጠም፡፡

በተመሳሳይም ነዋሪነቱ በአዲስ አበባ ከተማ የካ ከፍለ ከተማ የሆነው ግለሰብ እንደ ልጁ ያሳደጋትን የ15 ዓመት ታዳጊ በተለያየ ጊዜ በመድፈርና ለእርግዝና እንድትጋለጥ በማድረግ በእስራት መቀጣቱን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታወቀ፡፡

ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እንዳለው ግለሰቡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ጊዜያት በመኖሪያ ቤቱና ጥበቃ በሚሰራበት ቤት በታዳጊዋ ላይ በተደጋጋሚ አስገድዶ የመድፈር ጥቃት እንደፈጸመባት ገልጿል።

በዚህም ምክንያት ታዳጊዋ ለእርግዝና ተጋልጣለች። ይህንንም ተከትሎ ግለሰቡ እድሜዋ ባለደረሰ ታዳጊ ላይ ድርጊቱን በመፈጸሙ ክስ ቀርቦበት ነበር፡፡

ተከሳሹ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርቦ ድርጊቱን እንደፈጸመ እና ጥፋተኛ እንደሆነ ማመኑም ተገልጿል፡፡

ፍርድ ቤቱም ግለሰቡ ጥፋቱን በማመኑና ተጨማሪ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ በ11 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡

በተለይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ በህጻናት እና ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በአገር አቀፍም ሆነ በሌሎች የዓለም አገራት እየጨመረ መሆኑ ባለፉት ጥቂት ወራት የወጡ ሪፖርቶች አመልክተዋል።

ይህንን ጥቃት በመቃወምም በተለያዩ አገራት የተለያዩ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ሲሆን በኢትዮጵያም "ዝም አልልም" የሚል ጾታዊ ጥቃትን የሚቃወሙ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ነው፡፡

በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ብቻ በሁለት ወራት ከፍተኛ ቁትር ያላቸው ህጻናት ላይ አስገድዶ መድፈር ወንጀል እንደተፈጸመባቸው የሴችና ህጻናት ቢሮ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡